| ← Isaiah (64/66) → |
| 1. | ሰማዮችን ቀድደህ ምነው ብትወርድ! ተራሮችም ምነው ቢናወጡ! |
| 2. | እሳት ጭራሮውን እንደሚያቃጥል፥ እሳትም ውኃውን እንደሚያፈላ፥ ስምህ ለጠላቶችህ ይገለጥ ዘንድ፥ አሕዛብም በፊትህ ይንቀጠቀጡ ዘንድ። |
| 3. | ያልተጠባበቅነውን የክብርህን ሥራ ባደረግህ ጊዜ፥ ወረድህ ተራሮችም በፊትህ ተንቀጠቀጡ። |
| 4. | ሰዎች ከጥንት ጀምሮ ለሚጠብቁህ ከምትሠራላቸው ከአንተ በቀር ሌላ አምላክን አልሰሙም በጆሮአቸውም አልተቀበሉም ዓይንም አላየችም። |
| 5. | ጽድቅን የሚያደርገውን በመንገዶችህም የሚያስቡህን ትገናኛቸዋለህ። እነሆ፥ እነተ ተቈጣህ እኛም ኃጢአት ሠራን፤ ስለዚህም ተሳሳትን። |
| 6. | ሁላችን እንደ ርኩስ ሰው ሆነናል፥ ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው፤ ሁላችንም እንደ ቅጠል ረግፈናል፥ በደላችንም እንደ ነፋስ ወስዶናል። |
| 7. | ስምህንም የሚጠራ፥ አንተንም ሊይዝ የሚያስብ የለም፤ ፊትህንም ከእኛ ሰውረሃል፥ በኃጢአታችንም አጥፍተኸናል። |
| 8. | አሁን ግን፥ አቤቱ፥ አንተ አባታችን ነህ፤ እኛ ጭቃ ነን አንተም ሠሪያችን ነህ፥ እኛም ሁላችን የእጅህ ሥራ ነን። |
| 9. | አቤቱ፥ እጅግ አትቈጣ፥ ለዘላለምም ኃጢአትን አታስብ፤ እነሆ፥ እባክህ፥ ተመልከት፥ እኛ ሁላችን ሕዝብህ ነን። |
| 10. | የተቀደሱ ከተሞችህ ምድረ በዳ ሆነዋል፤ ጽዮን ምድረ በዳ ኢየሩሳሌምም ውድማ ሆናለች። |
| 11. | አባቶቻችን አንተን ያመሰገኑበት የተቀደሰና የተዋበ ቤታችን በእሳት ተቃጥሎአል፥ ያማረውም ስፍራችን ሁሉ ፈርሶአል። |
| 12. | አቤቱ፥ በውኑ በዚህ ነገር ትታገሣለህን? ዝምስ ትላለህን? አጥብቀህስ ታስጨንቀናለህን? |
| ← Isaiah (64/66) → |