← Isaiah (63/66) → |
1. | ይህ ከኤዶምያስ፥ ልብሱም የቀላ ከባሶራ የሚመጣ፥ አለባበሱ ያማረ፥ በጕልበቱ ጽናት የሚራመድ ማን ነው? በጽድቅ የምናገር ለማዳንም የምበረታ እኔ ነኝ። |
2. | ቀሚስህ ስለ ምን ቀላ? ልብስህስ በወይን መጥመቂያ እንደሚረግጥ ሰው ልብስ ስለ ምን መሰለ? |
3. | መጥመቂያውን ብቻዬን ረግጫለሁ፥ ከአሕዛብም አንድ ሰው ከእኔ ጋር አልነበረም፤ በቍጣዬ ረገጥኋቸው በመዓቴም ቀጠቀጥኋቸው፤ ደማቸውም በልብሴ ላይ ተረጭቶአል፥ ልብሴንም ሁሉ አስድፌአለሁ። |
4. | የምበቀልበት ቀን በልቤ ነውና፥ የምቤዥበትም ዓመት ደርሶአልና። |
5. | ተመለከትሁ፥ የሚረዳም አልተገኘም፤ የሚያግዝም አልነበረምና ተደነቅሁ፤ ስለዚህ የገዛ ክንዴ መድኃኒት አመጣልኝ፥ ቍጣዬም እርሱ አገዘኝ። |
6. | በቍጣዬም አሕዛብን ረገጥሁ በመዓቴም ቀጠቀጥኋቸው፥ ደማቸውንም ወደ ምድር አፈሰስሁት። |
7. | እግዚአብሔር እንደ ሰጠን ሁሉ፥ የእግዚአብሔርን ቸርነትና የእግዚአብሔርን ምስጋና፥ እንደ ምሕረቱና እንደ ቸርነቱም ብዛት ለእስራኤል ቤት የሰጠውን ትልቅ በጎነት አሳስባለሁ። |
8. | እርሱም። በእውነት ሕዝቤ፥ ሐሰትን የማያደርጉ ልጆች፥ ናቸው አለ፤ መድኃኒትም ሆነላቸው። |
9. | በጭንቃቸው ሁሉ እርሱ ተጨነቀ፥ የፊቱም መልአክ አዳናቸው፤ በፍቅሩና በርኅራኄውም ተቤዣቸው፥ በቀደመውም ዘመን ሁሉ አንሥቶ ተሸከማቸው። |
10. | እነርሱ ግን ዐመፁ ቅዱስ መንፈሱንም አስመረሩ፤ ስለዚህ ተመልሶ ጠላት ሆናቸው፥ እርሱም ተዋጋቸው። |
11. | እርሱም እንዲህ ብሎ የቀደመውን ዘመን አሰበ። የበጎቹን እረኛ ከባሕሩ ያወጣው ወዴት ነው ያለ? ቅዱስ መንፈሱንም በመካከላቸው ያኖረ ወዴት ነው ያለ? |
12. | የከበረውንም ክንድ በሙሴ ቀኝ ያስሄደ፥ ለራሱም የዘላለምን ስም ያደርግ ዘንድ ውኃውን በፊታቸው የከፈለ፥ |
13. | በምድረ በዳም እንደሚያልፍ ፈረስ፥ በቀላይ ውስጥ ያለ ዕንቅፋት ያሳለፋቸው ወዴት ነው ያለ? |
14. | ወደ ሸለቆ እንደሚወርዱ ከብቶች፥ እንዲሁ የእግዚአብሔር መንፈስ ወደ ዕረፍት አመጣቸው፤ እንዲሁም ለራስህ የከበረ ስም ታደርግ ዘንድ ሕዝብን መራህ። |
15. | ከሰማይ ተመልከት፥ ከቅዱስነትህና ከክብርህም ማደሪያ ጐብኝ፤ ቅንዓትህና ኃይልህስ ወዴት ነው? ለእኔም የሆነው የልብህ ናፍቆትና ርኅራኄህ ተከለከለ። |
16. | አብርሃም ባያውቀን እስራኤልም ባይገነዘበን አንተ አባታችን ነህ፤ አቤቱ፥ አንተ አባታችን ነህ፥ ስምህም ከዘላለም ታዳጊያችን ነው። |
17. | አቤቱ፥ ከመንገድህ ለምን አሳትኸን? እንዳንፈራህም ልባችንን ለምን አጸናህብን? ስለ ባሪያዎችህ ስለ ርስትህ ነገዶች ተመለስ። |
18. | የተቀደሰው ሕዝብህ መቅደስህን ጥቂት ጊዜ ወረሱት፤ ጠላቶቻችንም ረግጠውታል። |
19. | ከዘላለም እንዳልገዛኸን በስምህም እንዳልተጠራን ሆነናል። |
← Isaiah (63/66) → |