| ← Isaiah (61/66) → |
| 1. | የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፥ ለድሆች የምሥራችን እሰብክ ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና፤ ልባቸው የተሰበረውን እጠግን ዘንድ፥ ለተማረኩትም ነጻነትን ለታሰሩትም መፈታትን እናገር ዘንድ ልኮኛል። |
| 2. | የተወደደችውን የእግዚአብሔርን ዓመት አምላካችንም የሚበቀልበትን ቀን እናገር ዘንድ፥ የሚያለቅሱትንም ሁሉ አጽናና ዘንድ፤ |
| 3. | እግዚአብሔር ለክብሩ የተከላቸው የጽድቅ ዛፎች እንዲባሉ ለጽዮን አልቃሾች አደርግላቸው ዘንድ፥ በአመድ ፋንታ አክሊልን፥ በልቅሶም ፋንታ የደስታን ዘይት፥ በኀዘንም መንፈስ ፋንታ የምስጋናን መጐናጸፊያ እሰጣቸው ዘንድ ልኮኛል። |
| 4. | ከጥንትም ጀምሮ ባድማ የነበሩትን ይሠራሉ ከቀድሞ የፈረሱትንም ያቆማሉ፤ ባድማ የነበሩትንና ከብዙ ትውልድ በፊት የፈረሱትን ከተሞች እንደ ገና ይሠራሉ። |
| 5. | መጻተኞችም ቆመው በጎቻችሁን ያሰማራሉ፥ ሌሎች ወገኖችም አራሾችና ወይም ጠባቂዎች ይሆኑላችኋል። |
| 6. | እናንተ ግን የእግዚአብሔር ካህናት ትባላላችሁ፥ ሰዎቹም የአምላካችን አገልጋዮች ብለው ይጠሩአችኋል፤ የአሕዛብን ሀብት ትበላላችሁ፥ በክብራቸውም ትመካላችሁ። |
| 7. | በእፍረታችሁ ፋንታ ሁለት እጥፍ ይሆንላችኋል፥ በውርደታችሁም ፋንታ ዕድል ፈንታችሁ ደስ ይላቸዋል፤ ስለዚህ በምድራቸው ሁሉ እጥፍ ይገዛሉ፥ የዘላለምም ደስታ ይሆንላቸዋል። |
| 8. | እኔ እግዚአብሔር ፍርድን የምወድድ ስርቆትንና በደልን የምጠላ ነኝ፤ ፍዳቸውንም በእውነት እሰጣቸዋለሁ፥ ከእነርሱም ጋር የዘላለም ቃል ኪዳን አደርጋለሁ። |
| 9. | ዘራቸውም በአሕዛብ መካከል፥ ልጆቻቸውም በወገኖች መካከል የታወቁ ይሆናሉ፤ ያያቸው ሁሉ እግዚአብሔር የባረካቸው ዘር እንደ ሆኑ ይገነዘባል። |
| 10. | አክሊልን እንደ ለበሰ ሙሽራ፥ በጌጥ ሽልማትዋም እንዳጌጠች ሙሽራ፥ የማዳንን ልብስ አልብሶኛልና፥ የጽድቅንም መጐናጸፊያ ደርቦልኛልና በእግዚአብሔር እጅግ ደስ ይለኛል፥ ነፍሴም በአምላኬ ሐሤት ታደርጋለች። |
| 11. | ምድርም ቡቃያዋን እንደምታወጣ፥ ገነትም ዘሩን እንደሚያበቅል፥ እንዲሁ ጌታ እግዚአብሔር ጽድቅንና ምስጋናን በአሕዛብ ሁሉ ፊት ያበቅላል። |
| ← Isaiah (61/66) → |