| ← Isaiah (60/66) → |
| 1. | ብርሃንሽ መጥቶአልና፥ የእግዚአብሔርም ክብር ወጥቶልሻልና ተነሺ፥ አብሪ። |
| 2. | እነሆ፥ ጨለማ ምድርን ድቅድቅ ጨለማም አሕዛብን ይሸፍናል፤ ነገር ግን በአንቺ ላይ እግዚአብሔር ይወጣል ክብሩም በአንቺ ላይ ይታያል፤ |
| 3. | አሕዛብም ወደ ብርሃንሽ ነገሥታትም ወደ መውጫሽ ጸዳል ይመጣሉ። |
| 4. | ዓይኖችሽን አንሥተሽ በዙሪያሽ ተመልከቺ፤ እነዚህ ሁሉ ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ፤ ወንዶች ልጆችሽ ከሩቅ ይመጣሉ፥ ሴቶች ልጆችሽንም በጫንቃ ላይ ይሸከሙአቸዋል። |
| 5. | በዚያን ጊዜ የባሕሩ በረከት ወደ አንቺ ስለሚመለስ፥ የአሕዛብም ብልጥግና ወደ አንቺ ስለሚመጣ፥ አይተሽ ደስ ይልሻል፥ ልብሽም ይደነቃል ይሰፋማል። |
| 6. | የግመሎች ብዛት፥ የምድያምና የጌፌር ግመሎች፥ ይሸፍኑሻል፤ ሁሉ ከሳባ ይመጣሉ፥ ወርቅንና ዕጣንን ያመጣሉ የእግዚአብሔርንም ምስጋና ያወራሉ። |
| 7. | የቄዳር መንጎች ሁሉ ወደ አንቺ ይሰበሰባሉ የነባዮትም አውራ በጎች ያገለግሉሻል፤ እኔን ደስ ሊያሰኙ በመሠዊያዬ ላይ ይወጣሉ፥ የክብሬንም ቤት አከብራለሁ። |
| 8. | ርግቦች ወደ ቤታቸው እንደሚበርሩ፥ እነዚህ እንደ ደመና የሚበርሩ እነማን ናቸው? |
| 9. | እርሱ አክብሮሻልና ለአምላክሽ ለእግዚአብሔር ስምና ለእስራኤል ቅዱስ ልጆችሽን ከሩቅ ከእነርሱ ጋርም ብራቸውንና ወርቃቸውን ያመጡ ዘንድ ደሴቶች የተርሴስ መርከቦችም አስቀድመው ይጠባበቁኛል። |
| 10. | በቍጣዬ ቀሥፌ በፍቅሬ ምሬሻለሁና መጻተኞች ቅጥርሽን ይሠራሉ፥ ነገሥታቶቻቸውም ያገለግሉሻል። |
| 11. | በሮችሽም ሁልጊዜ ይከፈታሉ፤ ሰዎች የአሕዛብን ብልጥግና የተማረኩትንም ነገሥታቶቻቸውን ወደ አንቺ ያመጡ ዘንድ ሌሊትና ቀን አይዘጉም። |
| 12. | ለአንቺም የማይገዛ ሕዝብና መንግሥት ይጠፋል፥ እነዚያ አሕዛብም ፈጽመው ይጠፋሉ። |
| 13. | የመቅደሴንም ስፍራ ያስጌጡ ዘንድ የሊባኖስ ክብር፥ ጥዱና አስታው ባርሰነቱም፥ ወደ አንቺ ይመጣሉ፥ የእግሬንም ስፍራ አከብራለሁ። |
| 14. | የአስጨናቂዎችሽም ልጆች አንገታቸውን ደፍተው ወደ አንቺ ይመጣሉ፥ የናቁሽም ሁሉ ወደ እግርሽ ጫማ ይሰግዳሉ፤ የእግዚአብሔርም ከተማ፥ የእስራኤል ቅዱስ የሆንሽ ጽዮን ይሉሻል። |
| 15. | ከሰውም ማንም እስከማያልፍብሽ ድረስ የተተውሽና የተጠላሽ ነበርሽ፤ ነገር ግን የዘላለም ትምክሕትና የልጅ ልጅ ደስታ አደርግሻለሁ። |
| 16. | የአሕዛብንም ወተት ትጠጫለሽ የነገሥታትንም ጡት ትጠቢያለሽ፤ እኔም እግዚአብሔር የያዕቆብ ኃይል፥ መድኃኒትሽና ታዳጊሽ እንደ ሆንሁ ታውቂያለሽ። |
| 17. | በናስ ፋንታ ወርቅን፥ በብረትም ፋንታ ብርን፥ በእንጨትም ፋንታ ናስን፥ በድንጋይም ፋንታ ብረትን አመጣለሁ። አለቆችሽንም ሰላም፥ የበላይ ገዢዎችሽንም ጽድቅ አደርጋለሁ፤ |
| 18. | ከዚያ በኋላ በምድርሽ ውስጥ ግፍ፥ በዳርቻሽም ውስጥ ጕስቍልናና ቅጥቃጤ አይሰማም፤ ቅጥርሽን መዳን በሮችሽንም ምስጋና ብለሽ ትጠሪያለሽ |
| 19. | ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር የዘላለም ብርሃንሽ፥ አምላክሽም ክብርሽ ይሆናልና ፀሐይ በቀን ብርሃን አይሆንልሽም፥ የጨረቃም ብርሃን በሌሊት አይበራልሽም። |
| 20. | እግዚአብሔር የዘላለም ብርሃንሽ ይሆናልና፥ የልቅሶሽም ወራት ታልቃለችና ፀሐይሽ ከዚያ በኋላ አትጠልቅም ጨረቃሽም አይቋረጥም። |
| 21. | ሕዝብሽም ሁሉ ጻድቃን ይሆናሉ፤ እኔም እከብር ዘንድ የአታክልቴን ቡቃያ፥ የእጄ ሥራ የምትሆን ምድሪቱንም ለዘላለም ይወርሳሉ። |
| 22. | ታናሹ ለሺህ የሁሉም ታናሹ ለብርቱ ሕዝብ ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር በዘመኑ ይህን አፋጥነዋለሁ። |
| ← Isaiah (60/66) → |