| ← Isaiah (6/66) → |
| 1. | ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት፥ የልብሱም ዘርፍ መቅደሱን ሞልቶት ነበር። |
| 2. | ሱራፌልም ከእርሱ በላይ ቆመው ነበር፥ ለእያንዳንዱም ስድስት ክንፍ ነበረው፤ በሁለት ክንፍ ፊቱን ይሸፍን ነበር፥ በሁለቱም ክንፍ እግሮቹን ይሸፍን ነበር፥ በሁለቱም ክንፍ ይበር ነበር። |
| 3. | አንዱም ለአንዱ። ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች እያለ ይጮኽ ነበር። |
| 4. | የመድረኩም መሠረት ከጭዋኺው ድምፅ የተነሣ ተናወጠ፥ ቤቱንም ጢስ ሞላበት። |
| 5. | እኔም። ከንፈሮቼ የረከሱብኝ ሰው በመሆኔ፥ ከንፈሮቻቸውም በረከሱባቸው ሕዝብ መካከል በመቀመጤ ዓይኖቼ የሠራዊትን ጌታ ንጉሡን እግዚአብሔርን ስለ አዩ ጠፍቻለሁና ወዮልኝ! አልሁ። |
| 6. | ከሱራፌልም አንዱ እየበረረ ወደ እኔ መጣ፥ በእጁም ከመሠዊያው በጕጠት የወሰደው ፍም ነበረ። |
| 7. | አፌንም ዳሰሰበትና። እነሆ፥ ይህ ከንፈሮችህን ነክቶአል፤ በደልህም ከአንተ ተወገደ፥ ኃጢአትህም ተሰረየልህ አለኝ። |
| 8. | የጌታንም ድምፅ። ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል? ሲል ሰማሁ። እኔም። እነሆኝ፥ እኔን ላከኝ አልሁ። |
| 9. | እርሱም። ሂድ፥ ይህን ሕዝብ። መስማትን ትሰማላችሁ አታስተውሉምም፤ ማየትንም ታያላችሁ አትመለከቱምም በላቸው። |
| 10. | በዓይናቸው እንዳያዩ፥ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ ተመልሰውም እንዳይፈወሱ፥ የዚህን ሕዝብ ልብ አደንድን፥ ጆሮአቸውንም አደንቍር፥ ዓይናቸውንም ጨፍን አለኝ። |
| 11. | እኔም። ጌታ ሆይ፥ እስከ መቼ ድረስ ነው? አልሁ። እርሱም መልሶ እንዲህ አለ። ከተሞች የሚኖርባቸውን አጥተው እስኪፈርሱ ድረስ፥ ቤቶችም ሰው አልቦ እስኪሆኑ ምድርም ፈጽሞ ባድማ ሆና እስክትቀር ድረስ፥ |
| 12. | እግዚአብሔርም ሰዎችን እስኪያርቅ፥ በምድርም መካከል ውድማው መሬት እስኪበዛ ድረስ ነው። |
| 13. | በእርስዋም ዘንድ አሥረኛ እጅ ቀርቶ እንደ ሆነ እርሱ ደግሞ ይቃጠላል፤ በተቈረጡ ጊዜ ጉቶቻቸው እንደ ቀሩ እንደ ግራርና እንደ ኮምበል ዛፍ ሆኖ፥ ጉቶው የተቀደሰ ዘር ይሆናል። |
| ← Isaiah (6/66) → |