← Isaiah (57/66) → |
1. | ጻድቅ ይሞታል፥ በልቡም ነገሩን የሚያኖር የለም፤ ምሕረተኞችም ይወገዳሉ፥ ጽድቅም ከክፋት ፊት እንደ ተወገደ ማንም አያስተውልም። |
2. | ወደ ሰላም ይገባል፤ በቅንነት የሄደ በአልጋው ላይ ያርፋል። |
3. | እናንተ የአስማተኛይቱ ልጆች፥ የአመንዝራውና የጋለሞታይቱ ዘር፥ ወደዚህ ቅረቡ። |
4. | በማን ታላግጣላችሁ? በማንስ ላይ አፋችሁን ታላቅቃላችሁ? ምላሳችሁንስ በማን ላይ ታስረዝማላችሁ? |
5. | እናንተ በአድባር ዛፎች መካከል በለመለመም ዛፍ ሁሉ በታች በፍትወት የምትቃጠሉ፥ እናንተም በሸለቆች ውስጥ በዓለትም ስንጣቂዎች በታች ሕፃናትን የምታርዱ፥ የዓመፅ ልጆችና የሐሰት ዘር አይደላችሁምን? |
6. | በሸለቆው ውስጥ ያሉ የለዘቡ ድንጋዮች እድል ፈንታሽ ናቸው፥ እነርሱም ዕጣሽ ናቸው፤ ለእነርሱም የመጠጥ ቍርባን አፍስሰሻል፥ የእህልንም ቍርባን አቅርበሻል። እንግዲህ በዚህ ነገር አልቈጣምን? |
7. | ከፍ ባለውም በረዘመውም ተራራ ላይ መኝታሽን አደረግሽ፥ መሥዋዕትንም ትሠዊ ዘንድ ወደዚያ ወጣሽ። |
8. | ከመዝጊያውና ከመቃኑ በኋላ መታሰቢያሽን አደረግሽ፤ እኔን ትተሽ ለሌላ ተገልጠሻል፥ ወጥተሽ መኝታሽን አስፍተሻል፤ ቃል ኪዳንም ተጋባሻቸው፥ ባየሽበትም ስፍራ ሁሉ መኝታቸውን ወደድሽ። |
9. | ዘይትም ይዘሽ ወደ ንጉሡ ሄድሽ፥ ሽቱሽንም አበዛሽ፥ መልእክተኞችሽንም ወደ ሩቅ ላክሽ፥ እስከ ሲኦልም ድረስ ተዋረድሽ። |
10. | በመንገድሽም ብዛት ደከምሽ፥ ነገር ግን። ተስፋ የለም አላልሽም፤ የጕልበትን መታደስ አገኘሽ፥ ስለዚህም አልዛልሽም። |
11. | ሐሰትን የተናገርሺው እኔንም ያላሰብሺው በልብሽም ነገሩን ያላኖርሺው ማንን ሰግተሽ ነው? ማንንስ ፈርተሽ ነው? እኔ ብዙ ጊዜ ዝም አልሁ፥ አንቺም አልፈራሽም። |
12. | እኔ ጽድቅሽን እናገራለሁ፥ ሥራሽም አይረባሽም። |
13. | ወደ አንቺ የሰበሰብሻቸው በጮኽሽ ጊዜ ይታደጉሽ፤ ንፋስ ግን ይወስዳቸዋል ሽውሽውታም ሁሉን ያስወግዳቸዋል። በእኔ የታመነ ግን ምድሪቱን ይገዛል፥ የተቀደሰውንም ተራራዬን ይወርሳል። |
14. | እርሱም። ጥረጉ፥ መንገድን አዘጋጁ፥ ከሕዝቤም መንገድ ዕንቅፋትን አውጡ ይላል። |
15. | ለዘላለም የሚኖር ስሙም ቅዱስ የሆነ፥ ከፍ ያለው ልዑል እንዲህ ይላል። የተዋረዱትን ሰዎች መንፈስ ሕያው አደርግ ዘንድ፥ የተቀጠቀጠውንም ልብ ሕያው አደርግ ዘንድ፥ የተቀጠቀጠና የተዋረደ መንፈስ ካለው ጋር በከፍታና በተቀደሰ ስፍራ እቀመጣለሁ። |
16. | መንፈስም የፈጠርሁትም ነፍስ ከፊቴ እንዳይዝል ለዘላለም አልጣላም፥ ሁልጊዜም አልቈጣም። |
17. | ስለ ኃጢአቱ ጥቂት ጊዜ ተቈጥቼ ቀሠፍሁት፥ ፊቴን ሰውሬ ተቈጣሁ፤ እርሱም በልቡ መንገድ እያፈገፈገ ሄደ። |
18. | መንገዱን አይቻለሁ እፈውሰውማለሁ፥ እመራውማለሁ፥ ለእርሱና ስለ እርሱም ለሚያለቅሱ መጽናናትን እመልሳለሁ። |
19. | የከንፈሮችን ፍሬ እፈጥራለሁ፤ በሩቅም በቅርብም ላለው ሰላም ሰላም ይሁን፥ እፈውሰውማለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። |
20. | ክፉዎች ግን እንደሚንቀሳቀስ ባሕር ናቸው፤ ጸጥ ይል ዘንድ አይችልምና፥ ውኆቹም ጭቃና ጕድፍ ያወጣሉና። |
21. | ለክፉዎች ሰላም የላቸውም ይላል አምላኬ። |
← Isaiah (57/66) → |