| ← Isaiah (54/66) → |
| 1. | አንቺ ያልወለድሽ መካን ሆይ፥ ዘምሪ፤ አንቺ ያላማጥሽ ሆይ፥ እልል በዪ፥ ጩኺም፤ ባል ካላት ይልቅ ፈት የሆነቺቱ ልጆች በዝተዋልና፥ ይላል እግዚአብሔር። |
| 2. | የድንኳንሽን ስፍራ አስፊ፥ መጋረጃዎችሽንም ይዘርጉ፤ አትቈጥቢ፤ አውታሮችሽን አስረዝሚ ካስሞችሽንም አጽኚ። |
| 3. | በቀኝና በግራ ትሰፋፊያለሽና፥ ዘርሽም አሕዛብን ይወርሳልና፥ የፈረሱትንም ከተሞች መኖሪያ ያደርጋልና። |
| 4. | አታፍሪምና አትፍሪ፤ አተዋረጂምና አትደንግጪ፤ የሕፃንነትሽንም እፍረት ትረሺዋለሽ፥ የመበለትነትሽንም ስድብ ከእንግዲህ ወዲህ አታስቢም። |
| 5. | ፈጣሪሽ ባልሽ ነው፥ ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው፤ የእስራኤልም ቅዱስ ታዲጊሽ ነው፥ እርሱም የምድር ሁሉ አምላክ ይባላል። |
| 6. | እግዚአብሔር እንደ ተተወችና እንደ ተበሳጨች በልጅነትዋም እንደ ተጣለች ሚስት ጠርቶሻል፥ ይላል አምላክሽ። |
| 7. | ጥቂት ጊዜ ተውሁሽ፥ በታላቅም ምሕረት እሰበስብሻለሁ። |
| 8. | በጥቂት ቍጣ ለቅጽበት ዓይን ፊቴን ከአንቺ ሰወርሁ፥ በዘላለምም ቸርነት እምርሻለሁ፥ ይላል ታዳጊሽ እግዚአብሔር። |
| 9. | ይህ ለእኔ እንደ ኖኅ ውኃ ነው፤ የኖኅ ውኃ ደግሞ በምድር ላይ እንዳያልፍ እንደ ማልሁ፥ እንዲሁ አንቺን እንዳልቈጣ እንዳልዘልፍሽም ምያለሁ። |
| 10. | ተራሮች ይፈልሳሉ፥ ኮረብቶችም ይወገዳሉ፤ ቸርነቴ ግን ከአንቺ ዘንድ አይፈልስም የሰላሜም ቃል ኪዳን አይወገድም፥ ይላል መሐሪሽ እግዚአብሔር። |
| 11. | አንቺ የተቸገርሽ በዐውል ነፋስም የተናወጥሽ ያልተጽናናሽም፥ እነሆ፥ ድንጋዮችሽን ሸላልሜ እገነባለሁ፥ በሰንፔርም እመሠርትሻለሁ። |
| 12. | የግንብሽንም ጕልላት በቀይ ዕንቍ፥ በሮችሽንም በሚያብረቀርቅ ዕንቍ፥ ዳርቻሽንም ሁሉ በከበሩ ድንጋዮች እሠራለሁ። |
| 13. | ልጆችሽም ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፥ የልጆችሽም ሰላም ብዙ ይሆናል። |
| 14. | በጽድቅ ትታነጺያለሽ፤ ከግፍ ራቂ፥ አትፈሪምም፥ ድንጋጤም ወደ አንቺ አትቀርብም። |
| 15. | እነሆ፥ ይሰበሰባሉ፥ ነገር ግን ከእኔ ዘንድ አይሆንም፤ በአንቺም ላይ የሚሰበሰቡ ሁሉ ከአንቺ የተነሣ ይወድቃሉ። |
| 16. | እነሆ፥ ፍሙን በወናፍ የሚያናፋ ለሥራውም መሣሪያ የሚያወጣ ብረት ሠሪን እኔ ፈጥሬአለሁ፤ የሚያፈርሰውንም እንዲያጠፋ ፈጥሬአለሁ። |
| 17. | በአንቺ ላይ የተሠራ መሣሪያ ሁሉ አይከናወንም፤ በፍርድም በሚነሣብሽ ምላስ ሁሉ ትፈርጂበታለሽ። የእግዚአብሔር ባሪያዎች ርስት ይህ ነው፥ ጽድቃቸውም ከእኔ ዘንድ ነው፥ ይላል እግዚአብሔር። |
| ← Isaiah (54/66) → |