← Isaiah (52/66) → |
1. | ጽዮን ሆይ፥ ተነሺ፥ ተነሺ፥ ኃይልሽን ልበሺ፤ ቅድስቲቱ ከተማ ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ያልተገረዘና ርኩስ ከእንግዲህ ወዲህ አይገባብሽምና ጌጠኛ ልብስሽን ልበሺ። |
2. | ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ትቢያን አራግፊ፤ ተነሺ፥ ተቀመጪ፤ ምርኮኛይቱ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ የአንገትሽን እስራት ፍቺ። |
3. | እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በከንቱ ተሽጣችሁ ነበር፥ ያለ ገንዘብም ትቤዣላችሁ። |
4. | ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ወገኔ በዚያ እንግዳ ሆኖ ይቀመጥ ዘንድ አስቀድሞ ወደ ግብጽ ወረደ፥ አሦርም ያለ ምክንያት በደለው። |
5. | ወገኔ በከንቱ ተወስዶአልና አሁን ከዚህ ምን አለኝ? ይላል እግዚአብሔር፤ የሚገዙአቸው ይጮኻሉ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ስሜም ሁልጊዜ ቀኑን ሁሉ ይሰደባል። |
6. | ስለዚህ ወገኔ ስሜን ያውቃል፥ ስለዚህም የምናገር እኔ እንደ ሆንሁ በዚያ ቀን ያውቃሉ፤ እነሆ፥ እኔ ነኝ። |
7. | የምስራች የሚናገር፥ ሰላምንም የሚያወራ፥ የመልካምንም ወሬ የምስራች የሚናገር፥ መድኃኒትንም የሚያወራ፥ ጽዮንንም። አምላክሽ ነግሦአል የሚል ሰው እግሩ በተራሮች ላይ እጅግ ያማረ ነው። |
8. | እነሆ፥ ጕበኞችሽ ጮኸዋል፤ እግዚአብሔር ወደ ጽዮን በተመለሰ ጊዜ ዓይን በዓይን ይተያያሉና ድምፃቸውን ያነሣሉ፥ በአንድነትም ይዘምራሉ። |
9. | እናንተ የኢየሩሳሌም ፍርስራሾች ሆይ፥ እግዚአብሔር ሕዝቡን አጽናንቶአልና፥ ኢየሩሳሌምንም ታድጎአልና ደስ ይበላችሁ፥ በአንድነትም ዘምሩ። |
10. | እግዚአብሔር የተቀደሰውን ክንዱን በአሕዛብ ሁሉ ፊት ገልጦአል፥ በምድር ዳርቻ የሚኖሩትም ሁሉ የአምላካችንን መድኃኒት ያያሉ። |
11. | እናንተ የእግዚአብሔር ዕቃ የምትሸከሙ ሆይ፥ እልፍ በሉ፥ እልፍ በሉ፥ ከዚያ ውጡ፥ ርኩስን ነገር አትንኩ፥ ከመካከልዋ ውጡ፥ ንጽሐን ሁኑ። |
12. | እግዚአብሔር ይቀድማችኋልና፥ የእስራኤልም አምላክ ይከተላችኋልና በችኰላ አትወጡም በመኰብለልም አትሄዱም። |
13. | እነሆ፥ ባሪያዬ በማስተዋል ያደርጋል፤ ይከብራል ከፍ ከፍም ይላል፥ እጅግ ታላቅም ይሆናል። |
14. | ፊቱ ከሰዎች ሁሉ ይልቅ፥ መልኩም ከሰዎች ልጆች ይልቅ ተጐሳቍሎአልና ብዙ ሰዎች ስለ አንተ እንደ ተደነቁ፥ እንዲሁ ብዙ አሕዛብን ያስደንቃል፤ |
15. | ያልተነገረላቸውንም ያያሉና፥ ያልሰሙትንም ያስተውላሉና ነገሥታት ስለ እርሱ አፋቸውን ይዘጋሉ። |
← Isaiah (52/66) → |