| ← Isaiah (51/66) → |
| 1. | እናንተ ጽድቅን የምትከተሉ እግዚአብሔርንም የምትሹ፥ ስሙኝ፤ ከእርሱ የተቈረጣችሁበትን ድንጋይ ከእርሱም የተቈፈራችሁበትን ጕድጓድ ተመልከቱ። |
| 2. | ወደ አባታችሁ ወደ አብርሃም፥ ወደ ወለደቻችሁም ወደ ሳራ ተመልከቱ፤ አንድ ብቻውን በሆነ ጊዜ ጠራሁት፥ ባረክሁትም አበዛሁትም። |
| 3. | እግዚአብሔርም ጽዮንን ያጽናናል፤ በእርስዋም ባድማ የሆነውን ሁሉ ያጽናናል፥ ምድረ በዳዋንም እንደ ዔደን በረሀዋንም እንደ እግዚአብሔር ገነት ያደርጋል፤ ደስታና ተድላ ምስጋናና የዝማሬ ድምፅ ይገኝበታል። |
| 4. | ወገኔ ሆይ፥ አድምጠኝ፤ ሕዝቤ ሆይ፥ ስማኝ፤ ሕግ ከእኔ ይወጣልና ፍርዴም ለአሕዛብ ብርሃን ይሆናልና። |
| 5. | ጽድቄ ፈጥኖ ቀርቦአል፥ ማዳኔም ወጥቶአል፥ ክንዴም በአሕዛብ ላይ ይፈርዳል፤ ደሴቶች እኔን በመተማመን ይጠባበቃሉ፥ በክንዴም ይታመናሉ። |
| 6. | ዓይናችሁን ወደ ሰማይ አንሡ፥ ወደ ታችም ወደ ምድር ተመልከቱ፤ ሰማያት እንደ ጢስ በንነው ይጠፋሉ፥ ምድርም እንደ ልብስ ታረጃለች፥ የሚኖሩባትም እንዲሁ ይሞታሉ፤ ማዳኔ ግን ለዘላለም ይሆናል፥ ጽድቄም አይፈርስም። |
| 7. | ጽድቅን የምታውቁ ሕጌም በልባችሁ ያለ ሕዝብ ሆይ፥ ስሙኝ፤ የሰውን ተግዳሮት አትፍሩ፥ በስድባቸውም አትደንግጡ። |
| 8. | እንደ ልብስም ብል ይበላቸዋል፥ እንደ በግ ጠጕርም ትል ይበላቸዋል፤ ጽድቄ ግን ለዘላለም ማዳኔም ለትውልድ ሁሉ ይሆናል። |
| 9. | የእግዚአብሔር ክንድ ሆይ፥ ተነሥ፥ ተነሥ፥ ኃይልንም ልበስ፤ በቀድሞው ወራትና በጥንቱ ዘመን በነበረው ትውልድ እንደ ሆነው ተነሥ። ረዓብን የቈራረጥህ ዘንዶውንም የወጋህ አንተ አይደለህምን? |
| 10. | ባሕሩንና የታላቁን ጥልቅ ውኃ ያደረቅኸው፥ የዳኑትም ይሻገሩ ዘንድ ጠሊቁን ባሕር መንገድ ያደረግህ አንተ አይደለህምን? |
| 11. | እግዚአብሔርም የተቤዣቸው ይመለሳሉ ወደ ጽዮንም ይመጣሉ፤ የዘላለምም ደስታ በራሳቸው ላይ ይሆናል፤ ደስታንና ተድላን ያገኛሉ፥ ኀዘንና ልቅሶም ይሸሻል። |
| 12. | የማጽናናችሁ እኔ ነኝ፥ እኔ ነኝ፤ የሚሞተውን ሰው እንደ ሣርም የሚጠወልገውን የሰው ልጅ ትፈራ ዘንድ አንተ ማን ነህ? |
| 13. | ሰማያትንም የዘረጋው ምድርንም የመሠረተውን ፈጣሪህን እግዚአብሔርን ረስተሃል፤ ያጠፋ ዘንድ ባዘጋጀ ጊዜ ከአስጨናቂው ቍጣ የተነሣ ሁልጊዜ ቀኑን ሁሉ ፈርተሃል፤ የአስጨናቂው ቍጣ የት አለ? |
| 14. | ምርኮኛ ፈጥኖ ይፈታል፤ አይሞትም ወደ ጕድጓድም አይወርድም፥ እንጀራም አይጐድልበትም። |
| 15. | ሞገዱም እንዲተምም ባሕርን የማናውጥ አምላክህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ፥ ስሜም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው። |
| 16. | ሰማያትን እዘረጋ ዘንድ ምድርንም እመሠርት ዘንድ፥ ጽዮንንም። አንቺ ሕዝቤ ነሽ እል ዘንድ ቃሌን በአፍህ አድርጌአለሁ፥ በእጄም ጥላ ጋርጄሃለሁ። |
| 17. | ከእግዚአብሔር እጅ የቍጣውን ጽዋ የጠጣሽ ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ንቂ፥ ንቂ፥ ቁሚ፤ የሚያንገደግድን ዋንጫ ጠጥተሻል ጨልጠሽውማል። |
| 18. | ከወለደቻቸው ልጆች ሁሉ የሚመራት የለም፥ ካሳደገቻቸውም ልጆች ሁሉ እጅዋን የሚይዝ የለም። |
| 19. | እነዚህ ሁለት ነገሮች ሆነውብሻል፥ ማንስ ያስተዛዝንሻል? መፈታትና ጥፋት ራብና ሰይፍ ናቸው፤ እንዴትስ አድርጌ አጽናናሻለሁ? |
| 20. | ልጆችሽ ዝለዋል፤ በወጥመድ እንደተያዘ ሚዳቋ በአደባባይ ሁሉ ራስ ላይ ተኝተዋል፤ በእግዚአብሔር ቍጣና በአምላክሽ ተግሣጽ ተሞልተዋል። |
| 21. | ስለዚህም ያለ ወይን ጠጅ የሰከርሽ አንቺ ችግረኛ፥ ይህን ስሚ፤ |
| 22. | ስለ ወገኑ የሚምዋገት አምላክሽ ጌታሽ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ የሚያንገደግድን ጽዋ የቍጣዬንም ዋንጫ ከእጅሽ ወስጃለሁ፤ ደግመሽም ከእንግዲህ ወዲህ አትጠጪውም። |
| 23. | ነፍስሽንም። እንሻገር ዘንድ ዝቅ በዪ በሚሉአት በአስጨናቂዎችሽ እጅ አኖረዋለሁ፤ ጀርባሽንም ለሚሻገሩት እንደ መሬትና እንደ መንገድ አደረግሽላቸው። |
| ← Isaiah (51/66) → |