Isaiah (49/66)  

1. ደሴቶች ሆይ፥ ስሙኝ፥ እናንተም በሩቅ ያላችሁ አሕዛብ፥ አድምጡ፤ እግዚአብሔር ከማኅፀን ጠርቶኛል፥ ከእናቴም ሆድ ጀምሮ ስሜን አንሥቶአል፤
2. አፌንም እንደ ተሳለ ሰይፍ አድርጎአል፥ በእጁ ጥላ ሰውሮኛል፤ እንደ ተሳለ ፍላጻም አድርጎኛል፥ በሰገባውም ውስጥ ሽጎኛል።
3. እርሱም። እስራኤል ሆይ፥ አንተ ባሪያዬ ነህ በአንተም እከበራለሁ አለኝ።
4. እኔ ግን። በከንቱ ደከምሁ፥ ምንም ጥቅም ለሌለውና ለከንቱ ጕልበቴን ፈጀሁ፤ ፍርዴ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ፥ ዋጋዬም በአምላኬ ዘንድ ነው አልሁ።
5. አሁንም በእግዚአብሔር ዓይን ከብሬአለሁና፥ አምላኬም ጕልበት ሆኖኛልና ያዕቆብን ወደ እርሱ እንድመልስ እስራኤልንም ወደ እርሱ እንድሰበስብ ባሪያ እሆነው ዘንድ ከማኅፀን ጀምሮ የሠራኝ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል።
6. እርሱም። የያዕቆብን ነገዶች እንድታስነሣ ከእስራኤልም የዳኑትን እንድትመስል ባሪያዬ ትሆን ዘንድ እጅግ ቀላል ነገር ነውና እስከ ምድር ዳር ድረስ መድኃኒት ትሆን ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌ ሰጥቼሃለሁ ይላል።
7. የእስራኤል ታዳጊ ቅዱሱም፥ እግዚአብሔር፥ ሰዎች ለሚንቁት ሕዝብም ለሚጠላው ለገዥዎች ባሪያ እንዲህ ይላል። ስለ ታማኙ ስለ እግዚአብሔር ስለ መረጠህም ስለ እስራኤል ቅዱስ ነገሥታት አይተው ይነሣሉ፥ መሳፍንትም አይተው ይሰግዳሉ።
8. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በተወደደ ጊዜ ሰምቼሃለሁ፥ በመድኃኒትም ቀን ረድቼሃለሁ፤ እጠብቅህማለሁ፥ ምድርንም ታቀና ዘንድ፥ ውድማ የሆኑትንም ርስቶች ታወርስ ዘንድ፥
9. የተጋዙትንም። ውጡ በጨለማም የተቀመጡትን። ተገለጡ ትል ዘንድ ቃል ኪዳን አድርጌ ለሕዝቡ ሰጥቼሃለሁ። በመንገድም ላይ ይሰማራሉ፥ ማሰማርያቸውም በወና ኮረብታ ሁሉ ላይ ይሆናል።
10. የሚራራላቸውም ይመራቸዋልና፥ በውኃም ምንጮች በኩል ይነዳቸዋልና አይራቡም፥ አይጠሙም፥ ትኩሳት ወይም ፀሐይ አይጐዳቸውም።
11. ተራሮቼንም ሁሉ መንገድ አደርጋለሁ፥ ጎዳኖቼም ከፍ ከፍ ይላሉ።
12. እነሆ፥ እነዚህ ከሩቅ፥ እነሆም፥ እነዚህ ከሰሜንንና ከምዕራብ፥ እነዚህም ከሲኒም አገር ይመጣሉ።
13. እግዚአብሔር ሕዝቡን አጽናንቶአልና፥ ለችግረኞቹም ራርቶአልና ሰማያት ሆይ፥ ዘምሩ፥ ምድር ሆይ፥ ደስ ይበልሽ ተራሮችም ሆይ፥ እልል በሉ።
14. ጽዮን ግን። እግዚአብሔር ትቶኛል ጌታም ረስቶኛል አለች።
15. በውኑ ሴት ከማኅፀንዋ ለተወለደው ልጅ እስከማትራራ ድረስ ሕፃንዋን ትረሳ ዘንድ ትችላለችን? አዎን፥ እርስዋ ትረሳ ይሆናል፥ እኔ ግን አልረሳሽም።
16. እነሆ፥ እኔ በእጄ መጻፍ ቀርጬሻለሁ፥ ቅጥሮችሽም ሁልጊዜ በፊቴ አሉ።
17. ልጆችሽ ይፈጥናሉ፤ ያፈረሱሽና ያወደሙሽ ከአንቺ ዘንድ ይወጣሉ።
18. ዓይንሽን አንሥተሽ በዙሪያሽ ተመልከቺ፤ እነዚህ ሁሉ ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ። እኔ ሕያው ነኝና እነዚህን ሁሉ እንደ ጌጥ ትለብሻቸዋለሽ፥ እንደ ሙሽራም ትጐናጸፊአቸዋለሽ፥ ይላል እግዚአብሔር።
19. ባድማሽና ውድማሽ ወናም የሆነው ምድርሽ ከሚኖሩብሽ የተሣ ዛሬ ጠባብ ትሆናለችና፥ የዋጡሽም ይርቃሉና።
20. የወላድ መካን ከሆንሽ በኋላ የተወለዱልሽ ልጆችሽ በጆሮሽ። ስፍራ ጠብቦኛልና እቀመጥ ዘንድ ቦታ አስፊልኝ ይላሉ።
21. አንቺም በልብሽ፥ የወላድ መካን ሆኛለሁና፥ እኔም ብቻዬን ተሰድጄአለሁና ተቅበዝበዤ አለሁምና እነዚህን ማን ወለደልኝ? እነዚህንስ ማን አሳደጋቸው? እነሆ፥ ብቻዬን ቀርቼ ነበር፤ እነዚህስ ወዴት ነበሩ? ትያለሽ።
22. ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ እጄን ወደ አሕዛብ አነሣለሁ፥ ዓለማዬንም ወደ ወገኖች አቆማለሁ፤ ወንዶች ልጆችሽንም በብብታቸው ያመጡአቸዋል፥ ሴቶች ልጆችሽንም በጫንቃቸው ላይ ይሸከሙአቸዋል።
23. ነገሥታትም አሳዳጊ አባቶችሽ ይሆናሉ፥ እቴጌዎቻቸውም ሞግዚቶችሽ ይሆናሉ፤ ግምባራቸውንም ወደ ምድር ዝቅ አድርገው ይሰግዱልሻል፥ የእግርሽንም ትቢያ ይልሳሉ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቂያለሽ፥ እኔንም በመተማመን የሚጠባበቁ አያፍሩም።
24. በውኑ ብዝበዛ ከኃያል እጅ ይወሰዳልን? ወይስ የጨካኙ ምርኮኞች ያመልጣሉን?
25. እግዚአብሔር ግን እንዲህ ይላል። በኃያላን የተማረኩ ይወሰዳሉ፥ የጨካኞችም ብዝበዛ ያመልጣል፤ ከአንቺ ጋር የሚጣሉትን እጣላቸዋለሁ፥ ልጆችሽንም አድናለሁ።
26. አስጨናቂዎችሽንም ሥጋቸውን አስበላቸዋለሁ፥ እንደ ጣፋጭም ወይን ጠጅ ደማቸውን ጠጥተው ይሰክራሉ፤ ሥጋ ለባሹም ሁሉ እኔ እግዚአብሔር መድኃኒትሽና ታዳጊሽ፥ የያዕቆብ ኃያል እንደ ሆንሁ ያውቃል።

  Isaiah (49/66)