← Isaiah (48/66) → |
1. | እናንተ በእስራኤል ስም የተጠራችሁ ከይሁዳም ውኆች የወጣችሁ፥ በእግዚአብሔር ስም የምትምሉ፥ በእውነት ሳይሆን በጽድቅም ሳይሆን የእስራኤልን አምላክ የምትጠሩ፥ |
2. | በቅድስት ከተማ ስም የተጠራችሁ፥ ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በሚባል በእስራኤል አምላክ የምትደገፉ፥ የያዕቆብ ቤት ሆይ፥ ይህን ስሙ። |
3. | የቀድሞውን ነገር ከጥንት ተናግሬአለሁ፥ ከአፌም ወጥቶአል አሳይቼውማለሁ፤ ድንገት አድርጌዋለሁ ተፈጽሞማል። |
4. | አንተ እልከኛ፥ አንገትህም የብረት ጅማት፥ ግምባርህም ናስ እንደሆነ አውቄአለሁ፤ |
5. | ስለዚህ፥ አንተ። ጣዖቴ ይህን አድርጎአል፥ የተቀረጸው ምስሌና ቀልጦ የተሠራው ምስሌ ይህን አዘዙኝ እንዳትል፥ አስቀድሜ ነግሬህ ነበር ሳይሆንም አሳይቼህ ነበር። |
6. | ሰምተሃል፤ ይህን ሁሉ ተመልከት፤ እናንተም የምትናገሩት አይደላችሁምን? የተሰወሩትን ያላወቅሃቸውንም አዲሶች ነገሮችን ከዚህ ጀምሬ አሳይቼሃለሁ። |
7. | እነርሱም አሁን እንጂ ከጥንት አልተፈጠሩም፤ አንተም ። እነሆ፥ አውቄአቸዋለሁ እንዳትል ከዛሬ በፊት አልሰማሃቸውም። |
8. | አልሰማህም፥ አላወቅህም፥ ጆሮህ ከጥንት አልተከፈተችም፤ አንተ ፈጽሞ ወንጀለኛ እንደ ሆንህ ከማኅፀንም ጀምረህ ተላላፊ ተብለህ እንደተጠራህ አውቄአለሁና። |
9. | ስለ ስሜ ቍጣዬን አዘገያለሁ፥ እንዳላጠፋህም ስለ ምስጋናዬ እታገሣለሁ። |
10. | እነሆ፥ አንጥሬሃለሁ ነገር ግን እንደ ብር አይደለም፤ በመከራም እቶን ፈትኜሃለሁ። |
11. | ስለ እኔ፥ ስለ ራሴ አደርገዋለሁ ስሜ ተነቅፎአልና፤ ክብሬንም ለሌላ አልሰጥም። |
12. | ያዕቆብ ሆይ፥ የጠራሁህም እስራኤል ሆይ፥ ስማኝ፤ እኔ ነኝ፤ እኔ ፊተኛው ነኝ እኔም ኋለኛው ነኝ። |
13. | እጄም ምድርን መሥርታለች ቀኜም ሰማያትን ዘርግታለች፤ በጠራኋቸው ጊዜ በአንድነት ይቆማሉ። |
14. | እናንተ ሁሉ፥ በአንድነት ተሰብስባችሁ ስሙ፤ ከእነርሱ ይህን የተናገረ ማን ነው? እግዚአብሔር የወደደው ፈቃዱን በባቢሎን ላይ ያደርጋል፥ ክንዱም በከለዳውያን ላይ ይሆናል። |
15. | እኔ ራሴ ተናግሬአለሁ፤ እኔ ጠርቼዋለሁ፤ አምጥቼዋለሁ፥ መንገዱም ትከናወንለታለች። |
16. | ወደ እኔ ቅረቡ ይህንም ስሙ፤ እኔ ከጥንት ጀምሬ በስውር አልተናገርሁም፤ ከሆነበት ዘመን ጀምሮ እኔ በዚያ ነበርሁ፥ አሁንም ጌታ እግዚአብሔርና መንፈሱ ልከውኛል። |
17. | ታዳጊህ፥ የእስራኤል ቅዱስ፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ። እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ በምትሄድባትም መንገድ የምመራህ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ። |
18. | ትእዛዜን ብትሰማ ኖሮ፥ ሰላምህ እንደ ወንዝ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር፤ |
19. | ዘርህም እንደ አሸዋ የሆድህም ትውልድ እንደ ምድር ትቢያ በሆነ ነበር፥ ስሙም ከፊቴ ባልጠፋና ባልፈረሰ ነበር። |
20. | ከባቢሎን ውጡ ከከለዳውያንም ኰብልሉ፤ በእልልታ ድምፅ ተናገሩ ይህንም ንገሩ እስከ ምድርም ዳርቻ ድረስ አውሩና። እግዚአብሔር ባሪያውን ያዕቆብን ታድጎታል በሉ። |
21. | በምድረ በዳ በኩል በመራቸው ጊዜ አልተጠሙም፤ ውኃንም ከዓለቱ ውስጥ አፈለቀላቸው፥ ዓለቱንም ሰነጠቀ ውኃውም ፈሰሰ። |
22. | ለክፉዎች ሰላም የላቸውም ይላል እግዚአብሔር። |
← Isaiah (48/66) → |