Isaiah (47/66)  

1. አንቺ ድንግል የባቢሎን ልጅ ሆይ፥ ውረጂ በትቢያም ላይ ተቀመጪ፤ የከለዳውያን ሴት ልጅ ሆይ፥ ከዚህ በኋላ ቅልጣናምና ቅምጥል አትባይምና ያለ ዙፋን በመሬት ላይ ተቀመጪ።
2. ወፍጮ ወስደሽ ዱቄትን ፍጪ፤ መሸፈኛሽን አውጪ ረጅሙንም ልብስሽን አውልቀሽ ጣዪው፤ ባትሽን ግለጪ፥ ወንዙን ተሻገሪ።
3. ኀፍረተ ሥጋሽ ይገለጣል እፍረትሽም ይታያል፤ እኔ እበቀላለሁ፥ ለማንም አልራራም።
4. ታዳጊያችን፥ ስሙ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ የእስራኤል ቅዱስ ነው።
5. የከለዳውያን ሴት ልጅ ሆይ፥ ከዚህ በኋላ። የመንግሥታት እመቤት አትባይምና ዝም ብለሽ ተቀመጪ ወደ ጨለማም ውስጥ ግቢ።
6. በሕዝቤ ላይ ተቈጥቼ ነበር ርስቴንም አረከስሁ በእጅሽም አሳልፌ ሰጠኋቸው፤ ከእነርሱ ጋር ምሕረት አላደረግሽም፥ በሽማግሌዎቻቸው ላይ ቀንበርሽን እጅግ አክብደሻል።
7. አንቺም። እኔ ለዘላለም እመቤት እሆናለሁ ብለሻል፤ ይህንም በልብሽ አላደረግሽም ፍጻሜውንም አላሰብሽም።
8. አሁንም አንቺ ቅምጥል ተዘልለሽ የምትቀመጪ፥ በልብሽም። እኔ ነኝ ከእኔም በቀር ሌላ የለም፤ መበለትም ሆኜ አልኖርም የወላድ መካንነትንም አላውቅም የምትዪ ይህን ስሚ፤
9. አሁን ግን በአንድ ቀን እነዚህ ሁለት ነገሮች፥ የወላድ መካንነትና መበለትነት፥ በድንገት ይመጡብሻል፤ ስለ መተቶችሽ ብዛትና ስለ አስማቶችሽ ጽናት ፈጽመው ይመጡብሻል።
10. በክፋትሽ ታምነሻል፤ የሚያየኝ የለም ብለሻል፤ ጥበብሽና እውቀትሽ አታልለውሻል፥ በልብሽም። እኔ ነኝ ከእኔም በቀር ሌላ የለም ብለሻል።
11. ስለዚህ ምክንያት ክፉ ነገር ይመጣብሻል፥ በምዋርትሽም እንዴት እንደምታርቂው አታውቂም፤ ጉዳት ይውድቅብሻል ታስወግጅውም ዘንድ አይቻልሽም፤ የማትውቂያትም ጕስቍልና ድንገት ትመጣብሻለች።
12. ምናልባትም መጠቀም ትችዪ ወይም ታስደነግጪ እንደ ሆነ፥ ከአስማቶችሽና ከሕፃንነትሽ ጀምረሽ ከደከምሽበት ከመተቶችሽ ብዛት ጋር ቁሚ።
13. በምክርሽ ብዛት ደክመሻል፤ አሁንም የሰማይን ከዋክብት የሚቈጥሩ፥ ከዋክብትንም የሚመለከቱ፥ በየመባቻውም የሚመጣውን ነገር የሚናገሩ ተነሥተው ከሚመጣብሽ ነገር ያድኑሽ።
14. እነሆ፥ እንደ እብቅ ይሆናሉ፥ እሳትም ያቃጥላቸዋል ሰውነታቸውንም ከነበልባል ኃይል አያድኑም፤ እርሱም ሰው እንደሚሞቀው ፍም፥ ወይም በፊቱ ሰው እንደሚቀመጥበት እሳት ያለ አይደለም።
15. የደከምሽባቸው ነገሮች እንዲህ ይሆኑብሻል፤ ከሕፃንነትሽ ጀምረው ከአንቺ ጋር ይነግዱ የነበሩ እያንዳንዳቸው ወደ ስፍራቸው ይሄዳሉ፥ የሚያድንሽም የለም።

  Isaiah (47/66)