| ← Isaiah (42/66) → |
| 1. | እነሆ ደግፌ የያዝሁት ባሪያዬ፤ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ምርጤ፤ በእርሱ ላይ መንፈሴን አድርጌአለሁ፥ እርሱም ለአሕዛብ ፍርድን ያወጣል። |
| 2. | አይጮኽም ቃሉንም አያነሣም፥ ድምፁንም በሜዳ አያሰማም። |
| 3. | የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም፥ የሚጤስንም ክር አያጠፋም፤ በእውነት ፍርድን ያወጣል። |
| 4. | በምድርም ፍርድን እስኪያደርግ ድረስ ይበራል እንጂ አይጠፋም፤ አሕዛብም በስሙ ይታመናሉ። |
| 5. | ሰማያትን የፈጠረ የዘረጋቸውም፥ ምድርንና በውስጥዋ ያለውን ያጸና፥ በእርስዋ ላይ ለሚኖሩ ሕዝብ እስትንፋስን፥ ለሚሄዱባትም መንፈስን የሚሰጥ አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። |
| 7. | እኔ እግዚአብሔር በጽድቅ ጠርቼሃለሁ፥ እጅህንም እይዛለሁ እጠብቅህማለሁ፥ የዕውሩንም ዓይን ትከፍት ዘንድ የተጋዘውንም ከግዞት ቤት በጨለማም የተቀመጡትን ከወህኒ ቤት ታወጣ ዘንድ ለሕዝብ ቃል ኪዳን ለአሕዛብም ብርሃን አድርጌ እሰጥሃለሁ። |
| 8. | እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ስሜ ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ፥ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም። |
| 9. | እነሆ፥ የቀድሞው ነገር ተፈጸመ፥ አዲስ ነገርንም እናገራለሁ፤ አስቀድሞም ሳይበቅል እርሱን አስታውቃችኋለሁ። |
| 10. | ወደ ባሕር የምትወርዱ በእርስዋም ውስጥ ያላችሁ ሁሉ፥ ደሴቶችና በእነርሱም ላይ የምትኖሩ ሆይ፥ ለእግዚአብሔር አዲስ መዝሙር፥ ከምድርም ዳርቻ ምስጋናውን ዘምሩ። |
| 11. | ምድረ በዳውና ከተሞቹ የቄዳርም ሰዎች የሚቀመጡባቸው መንደሮች ድምፃቸውን ያንሡ፤ በሴላ የሚኖሩ እልል ይበሉ፥ በተራሮችም ራስ ላይ ሆነው ይጩኹ። |
| 12. | ለእግዚአብሔር ክብርን ይስጡ፥ ምስጋናውንም በደሴቶች ይናገሩ። |
| 13. | እግዚአብሔር እንደ ኃያል ይወጣል እንደ ሰልፈኛም ቅንዓትን ያስነሣል፤ ይጮኻል ድምፁንም ያሰማል በጠላቶቹም ላይ ይበረታል። |
| 14. | ከድሮ ዘመን ጀምሮ ዝም ብያለሁ፥ ዝም ብዬም ታግሻለሁ፤ አሁን ምጥ እንደ ያዛት ሴት እጮኻለሁ፤ አጠፋለሁ በአንድነትም እጨርሳለሁ። |
| 15. | ተራሮችንና ኮረብቶችን አፈርሳለሁ፥ ቡቃያዎቻቸውንም ሁሉ አደርቃለሁ፤ ወንዞችንም ደሴቶች አደርጋለሁ፥ ኵሬዎችንም አደርቃለሁ። |
| 16. | ዕውሮችንም በማያውቋት መንገድ አመጣቸዋለሁ፥ በማያውቋትም ጎዳና እመራቸዋለሁ፤ በፊታቸውም ጨለማውን ብርሃን አደርጋለሁ፥ ጠማማውንም አቀናለሁ። ይህን አደርግላቸዋለሁ፥ አልተዋቸውምም። |
| 17. | በተቀረጹትም ምስሎች የሚታመኑ፥ ቀልጠው የተሠሩትንም ምስሎች። አምላኮቻችን ናችሁ የሚሉ ወደ ኋላቸው ይመለሳሉ ፈጽመውም ያፍራሉ። |
| 18. | እናንተ ደንቆሮች፥ ስሙ፤ እናንተም ዕውሮች፥ ታዩ ዘንድ ተመልከቱ። |
| 19. | ከባሪያዬ በቀር ዕውር ማን ነው? እንደምልከው መልእክተኛዬስ በቀር ደንቆሮ የሆነ ማን ነው? እንደ ፍጹሙ ወይስ እንደ እግዚአብሔር ባሪያ ዕውር የሆነ ማን ነው? |
| 20. | ብዙ ነገርን ታያላችሁ ነገር ግን አትጠባበቁትም፤ ጆሮአችሁም ተከፍተዋል፥ ነገር ግን አትሰሙም። |
| 21. | እግዚአብሔር ስለ ጽድቁ ሕጉን ታላቅ ያደርግና ያከብር ዘንድ ወደደ። |
| 22. | ይህ ግን የተበዘበዘና የተዘረፈ ሕዝብ ነው፤ ሁላቸው በዋሻ ውስጥ ተጠምደዋል በግዞት ቤትም ተሸሽገዋል፤ ብዝበዛ ሆነዋል የሚያድንም የለም፥ ምርኮም ሆነዋል፥ ማንም። መልሱ አይልም። |
| 23. | ከመካከላችሁ ይህን የሚያደምጥ፥ ለሚመጣውም ጊዜ የሚያደምጥና የሚሰማ ማን ነው? |
| 24. | ያዕቆብን ለማረኩ እስራኤልንም ለበዘበዙ ሰዎች የሰጠ ማን ነው? እኛ የበደልነው፥ እነርሱም በመንገዱ ይሄዱ ዘንድ ያልወደዱት ለሕጉም ያልታዘዙለት እግዚአብሔር እርሱ አይደለምን? |
| 25. | ስለዚህ የቍጣውን መዓትና የሰልፉን ጽናት አፈሰሰበት፤ በዙሪያም አነደደው እርሱ ግን አላወቀም፥ አቃጠለውም እርሱ ግን ልብ አላደረገም። |
| ← Isaiah (42/66) → |