← Isaiah (38/66) → |
1. | በዚያም ወራት ሕዝቅያስ ለሞት እስኪደርስ ታመመ። ነቢዩም የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ወደ እርሱ መጥቶ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ትሞታለህ እንጂ በሕይወት አትኖርምና ቤትህን አስተካክል አለው። |
2. | ሕዝቅያስም ፊቱን ወደ ግድግዳው መልሶ እንዲህ ሲል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። |
3. | አቤቱ፥ በፊትህ በእውነትና በፍጹም ልብ እንደ ሄድሁ ደስ የሚያሰኝህንም እንዳደረግሁ ታስብ ዘንድ እለምንሃለሁ። ሕዝቅያስም እጅግ አድርጎ አለቀሰ። |
4. | የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል መጣ። |
5. | ሂድ፥ ሕዝቅያስን እንዲህ በለው። የአባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጸሎትህን ሰምቻለሁ፥ እንባህንም አይቻለሁ፤ እነሆ፥ በዕድሜህ ላይ አሥራ አምስት ዓመት አጨምራለሁ። |
6. | አንተንና ይህችንም ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ እታደጋለሁ፥ ይህችንም ከተማ እጋርዳታለሁ። |
7. | እግዚአብሔርም የተገረውን ነገር እንዲፈጽመው ከእግዚአብሔር ዘንድ ምልክቱ ይህ ይሆንልሃል። |
8. | እነሆ፥ በአካዝ የጥላ ስፍረ ሰዓት ላይ ከፀሐይ ጋር የወረደውን በደረጃዎች ያለውን ጥላ አሥር ደረጃ ወደ ኋላ እንዲመለስ አደርጋለሁ። ፀሐይም በጥላ ስፍረ ሰዓት ላይ የወረደበት አሥር ደረጃ ወደ ኋላ ተመለሰ። |
9. | የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ታምሞ ከደዌው በተፈወሰ ጊዜ የጻፈው ጽሕፈት ይህ ነው። |
10. | እኔ። በሕይወት ዘመኔ መካከል ወደ ሲኦል በሮች እገባለሁ፤ የቀረው ዘመኔ ጐደለብኝ አልሁ። |
11. | ደግሞም። በሕያዋን ምድር እግዚአብሔርን አላይም፤ በዓለምም ከሚኖሩ ጋር ሰውን እንግዲህ አልመለከትም አልሁ። |
12. | ማደሪያዬ ተነቀለች፥ እንደ እረኛ ድንኳንም ከእኔ ዘንድ ተወገደች፤ ሕይወቴንም እንደ ሸማኔ ጠቀለልሁ፥ እርሱም ከመጠቅለያው ይቈርጠኛል፤ ከማለዳም ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ታጠፋኛለህ። |
13. | እስኪነጋ ድረስ ቈይቼ ነበር፤ እርሱ እንደ አንበሳ አጥንቴን ሁሉ ሰበረ፤ ከማለዳ ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ታጠፋኛለህ። |
14. | እንደ ጨረባና እንደ ሽመላ ተንጫጫሁ፥ እንደ ርግብም አጕረመረምሁ፤ ዓይኖቼ ወደ ላይ ከማየት ደከሙ። ጌታ ሆይ፥ ተጨንቄአለሁና መከታ ሁነኝ። |
15. | ምን እላለሁ? እርሱ ተናግሮኛል፥ እርሱ ራሱም ይህን አድርጎአል፤ በዘመኔ ሁሉ ስለ ነፍሴ ምሬት ቀስ ብዬ እሄዳለሁ። |
16. | ጌታ ሆይ፥ በዚህ ነገር ሰዎች በሕይወት ይኖራሉ፥ በዚህም ሁሉ የመንፈሴ ሕይወት ነው፤ አንተም ፈወስኸኝ ወደ ሕይወትም መለስኸኝ። |
17. | እነሆ፥ ታላቅ ምሬት ለደኅንነቴ ሆነ፤ አንተም ነፍሴን ከጥፋት ጕድጓድ አዳንሃት፥ ኃጢአቴንም ሁሉ ወደ ኋላህ ጣልህ። |
18. | ሲኦል አያመሰግንህምና፥ ሞትም አያከብርህምና፤ ወደ ጕድጓዱ የሚወርዱ እውነትህን ተስፋ አያደርጉም። |
19. | እኔ ዛሬ አንደማደርግ ሕያዋን እነርሱ ያመሰግኑሃል፤ አባት ለልጆች እውነትህን ያስታውቃል። |
20. | እግዚአብሔር ያድነኛል፤ ስለዚህ በዕድሜያችን ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት ቅኔዎችን አውታር ባለው ዕቃ እንዘምራለን። |
21. | ኢሳይያስም። የበለስ ጥፍጥፍ አምጥተው በእባጩ ላይ ይለብጡት፥ እርሱም ይፈወሳል ብሎ ነበር። |
22. | ሕዝቅያስም። ወደ እግዚአብሔር ቤት እወጣ ዘንድ ምልክቱ ምንድር ነው? ብሎ ነበር። |
← Isaiah (38/66) → |