| ← Isaiah (37/66) → |
| 1. | እንዲህም ሆነ፤ ንጉሡ ሕዝቅያስ ይህን በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ፥ ማቅም ለበሰ፥ ወደ እግዚአብሔርም ቤት ገባ። |
| 2. | የቤቱንም አዛዥ ኤልያቄምን ጸሐፊውንም ሳምናስን የካህናቱንም ሽማግሌዎች ማቅ ለብሰው ወደ ነቢዩ ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ኢሳይያስ ይሄዱ ዘንድ ላካቸው። |
| 3. | እነርሱም። ሕዝቅያስ እንዲህ ይላል። ይህ ቀን የመከራና የተግሣጽ የዘለፋም ቀን ነው፤ ልጆች የሚወለዱበት ጊዜ ደርሶአል ለመውለድም ኃይል የለም። |
| 4. | ምናልባት በሕያው አምላክ ላይ ይገዳደር ዘንድ ጌታው የአሦር ንጉሥ የላከውን የራፋስቂስን ቃል አምላክህ እግዚአብሔር ይሰማ እንደ ሆነ፥ አምላክህ እግዚአብሔር ስለ ሰማው ቃል ይገሥጸው እንደ ሆነ፥ ስለዚህ ለቀረው ቅሬታ ጸልይ አሉት። |
| 5. | እንዲሁ የንጉሡ የሕዝቅያስ ባሪያዎች ወደ ኢሳይያስ መጡ። |
| 6. | ኢሳይያስም። ለጌታችሁ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የአሦር ንጉሥ ባሪያዎች ስለ ሰደቡኝ፥ ስለ ሰማኸው ቃል አትፍራ። |
| 7. | እነሆ፥ በላዩ መንፈስን እሰድዳለሁ፥ ወሬንም ይሰማል፥ ወደ ምድሩም ይመለሳል፤ በምድሩም በሰይፍ እንዲወድቅ አደርጋለሁ በሉት አላቸው። |
| 8. | የአሦርም ንጉሥ ከለኪሶ እንደ ራቀ ሰምቶ ነበርና ራፋስቂስ ተመልሶ በልብና ሲዋጋ አገኘው። |
| 9. | እርሱም። የኢትዮጵያ ንጉሥ ቲርሐቅ ሊዋጋህ መጥቶአል የሚል ወሬ ሰማ። በሰማም ጊዜ ወደ ሕዝቅያስ መልእክተኞችን ላከ፥ |
| 10. | እንዲህ ሲል። ለይሁዳ ንጉሠ ለሕዝቅያስ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት። ኢየሩሳሌም በአሦር ንጉሥ እጅ አትሰጥም ብሎ የምትታመንበት አምላክህ አያታልልህ። |
| 11. | እነሆ፥ የአሦር ነገሥታት በምድር ሁሉ ላይ ያደረጉትን፥ እንዴትስ እንዳጠፉአቸው ሰምተሃል፤ አንተስ ትድናለህን? |
| 12. | አባቶቼ ያጠፉአቸውን ጎዛንን፥ ካራንን፥ ራፊስን፥ በተላሳር የነበሩትንም የዔድንን ልጆች የአሕዛብ አማልክት አዳኑአቸውን? |
| 13. | የሐማት ንጉሥ፥ የአርፋድ ንጉሥ፥ የሴፈርዋይም ከተማ ንጉሥ፥ የሄናና የዒዋ ንጉሥ ወዴት አሉ? |
| 14. | ሕዝቅያስም ደብዳቤውን ከመልእክተኞች እጅ ተቀብሎ አነበበው፤ ሕዝቅያስም ወደ እግዚአብሔር ቤት ወጥቶ በእግዚአብሔር ፊት ዘረጋው። |
| 15. | ሕዝቅያስም ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ጸለየ። |
| 16. | አቤቱ፥ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ አንተ ብቻህን የምድር መንግሥታት ሁሉ አምላክ ነህ፤ ሰማይንና ምድርን ፈጥረሃል። |
| 17. | አቤቱ፥ ጆሮህን አዘንብልና ስማ፤ አቤቱ፥ ዓይንህን ክፈትና እይ፤ በሕያው አምላክ ላይ ይገዳደር ዘንድ የላከውን የሰናክሬም ቃል ስማ። |
| 18. | አቤቱ፥ በእውነት የአሦር ነገሥታት ዓለሙን ሁሉ አገሮቻቸውንም አፍርሰዋል፥ |
| 19. | አማልክቶቻቸውንም በእሳት ላይ ጥለዋል፤ የእንጨትና የድንጋይ የሰው እጅ ሥራ ነበሩ እንጂ አማልክት አልነበሩምና ስለዚህ አጥፍተዋቸዋል። |
| 20. | እንግዲህም አምላካችን አቤቱ፥ የምድር መንግሥታት ሁሉ አንተ ብቻ እግዚአብሔር እንደ ሆንህ ያውቁ ዘንድ ከእጁ አድነን። |
| 21. | የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ እንዲህ ብሎ ወደ ሕዝቅያስ ላከ። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ስለ አሦር ንጉሥ ስለ ሰናክሬም ወደ እኔ ለምነሃልና |
| 22. | እግዚአብሔር ስለ እርሱ የተናገረው ቃል ይህ ነው። ድንግሊቱ የጽዮን ልጅ ቀላል አድርጋሃለች፥ በንቀትም ስቃብሃለች፤ የኢየሩሳሌም ልጅ ራስዋን ነቅንቃብሃለች። |
| 23. | የተገዳደርኸው የሰደብኸውስ ማን ነው? ቃልህንስ ከፍ ከፍ ያደረግህበት ዓይንህንስ ወደ ላይ ያነሣህበት ማን ነው? በእስራኤል ቅዱስ ላይ ነው። |
| 24. | አንተም። በሰረገላዬ ብዛት ወደ ተራሮች ከፍታ፥ ወደ ሊባኖስ ጥግ ላይ ወጥቻለሁ፤ ረጃጅሞቹንም ዝግባዎች የተመረጡትንም ጥዶች እቈርጣለሁ፥ ወደ ከፍታውም ዳርቻ ወደ ቀርሜሎስ ዱር እገባለሁ። |
| 25. | ቈፈርሁም ውኃም ጠጣሁ የግብጽንም ወንዞች ሁሉ በእግሬ ጫማ አደርቃለሁ ብለህ በባሪያዎችህ እጅ በጌታ ላይ ተገዳደርህ። |
| 26. | እኔ ጥንቱን እንደ ሠራሁት፥ ቀድሞውንም እንዳደረግሁት አልሰማህምን? አሁንም የተመሸጉትን ከተሞች የፍርስራሽ ክምር እስኪሆኑ ድረስ እንድታፈርስ አደረግሁህ። |
| 27. | ስለዚህ የሚኖሩባቸው ሰዎች እጃቸው ዝሎአል፥ ደንግጠውም ታውከዋል፤ እንደ ምድረ በዳ ሣር፥ እንደ ለመለመም ቡቃያ፥ በሰገነትም ላይ እንዳለ ሣር፥ ሳይሸት ዋግ እንደ መታው እህል ሆነዋል። |
| 28. | እኔ ግን መቀመጫህንና መውጫህን መግቢያህንም በእኔም ላይ የተቈጣኸውን ቍጣ አውቄአለሁ። |
| 29. | ቍጣህና ትዕቢትህ ወደጆሮዬ ደርሶአልና ስለዚህ ስናጋዬን በአፍንጫህ ልጓሜንም በከንፈርህ አደርጋለሁ፥ በመጣህበትም መንገድ እመልስሃለሁ። |
| 30. | ይህም ምልክት ይሆንሃል፤ በዚህ ዓመት የገቦውን፥ በሁለተኛውም ዓመት ከገቦው የበቀለውን ትበላላችሁ፤ በሦስተኛውም ዓመት ትዘራላችሁ ታጭዱማላችሁ፥ ወይንም ትተክላላችሁ ፍሬውንም ትበላላችሁ። |
| 31. | ያመለጠው የይሁዳ ቤት ቅሬታ ሥሩን ወደ ታች ይሰድዳል፥ ወደ ላይም ያፈራል። |
| 32. | ከኢየሩሳሌም ቅሬታ ከጽዮንም ተራራ ያመለጡት ይወጣሉና፤ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቅንዓት ይህን ያደርጋል። |
| 33. | ስለዚህም እግዚአብሔር ስለ አሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል። ወደዚች ከተማ አይመጣም፥ ፍላጻንም አይወረውርባትም፥ በጋሻም አይመጣባትም፥ የአፈርንም ድልድል አይደለድልባትም። |
| 34. | በመጣበት መንገድ በዚያው ይመለሳል፥ ወደዚችም ከተማ አይመጣም ይላል እግዚአብሔር። |
| 35. | ስለ እኔም ስለ ባሪያዬም ስለ ዳዊት ይህችን ከተማ አድናት ዘንድ እጋርዳታለሁ። |
| 36. | የእግዚአብሔርም መልአክ ወጣ፥ ከአሦራውያንም ሰፈር መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ገደለ፤ ማለዳም በተነሡ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሁሉ በድኖች ነበሩ። |
| 37. | የአሦርም ንጉሥ ሰናክሬም ተነሥቶ ሄደ፥ ተመልሶም በነነዌ ተቀመጠ። |
| 38. | በአምላኩም በናሳራክ ቤት ሲሰግድ ልጆቹ አድራሜሌክና ሳራሳር በሰይፍ ገደሉት፤ ወደ አራራትም አገር ኰበለሉ። ልጁም አስራዶን በእርሱ ፋንታ ነገሠ። |
| ← Isaiah (37/66) → |