Isaiah (35/66)  

1. ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ደስ ይላቸዋል፥ በረሀውም ሐሤት ያደርጋል እንደ ጽጌ ረዳም ያብባል።
2. እጅግ ያብባል በደስታና በዝማሬ ሐሤትን ያደርጋል፤ የሊባኖስ ክብር፥ የቀርሜሎስና የሳሮን ግርማ ይሰጠዋል፤ የእግዚአብሔርንም ክብር የአምላካችንንም ግርማ ያያሉ።
3. የደከሙትን እጆች አበርቱ፥ የላሉትንም ጕልበቶች አጽኑ።
4. ፈሪ ልብ ላላቸው። እነሆ፥ አምላካችሁ በበቀል በእግዚአብሔርም ብድራት ይመጣልና፥ መጥቶም ያድናችኋልና በርቱ፥ አትፍሩ በሉአቸው።
5. በዚያን ጊዜም የዕውሮች ዓይን ይገለጣል፤ የደንቆሮችም ጆሮ ይከፈታል።
6. በዚያን ጊዜ አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘልላል፥ የድዳም ምላስ ይዘምራል፤ በምድረ በዳ ውኃ፥ በበረሀም ፈሳሽ ይፈልቃልና።
7. ደረቂቱ ምድር ኵሬ፥ የጥማት መሬት የውኃ ምንጭ ትሆናለች፤ ቀበሮ የተኛበት መኖሪያ ልምላሜና ሸምበቆ ደንገልም ይሆንበታል።
8. በዚያም ጐዳናና መንገድ ይሆናል እርሱም የተቀደሰ መንገድ ይባላል፤ ንጹሐንም ያልሆኑ አያልፉበትም፥ ለንጹሐን ግን ይሆናል፤ ተላላፊዎችና ሰነፎች እንኳ አይስቱበትም።
9. አንበሳም አይኖርበትም፥ ነጣቂ አውሬም አይወጣበትም፥ ከዚያም አይገኙም፤ የዳኑት ግን በዚያ ይሄዳሉ፤
10. እግዚአብሔርም የተቤዣቸው ይመለሳሉ እየዘመሩም ወደ ጽዮን ይመጣሉ፤ የዘላለም ደስታ በራሳቸው ላይ ይሆናል፤ ሐሤትንና ደስታን ያገኛሉ፥ ኀዘንና ትካዜም ይሸሻሉ።

  Isaiah (35/66)