← Isaiah (34/66) → |
1. | እናንተ አሕዛብ ሆይ፥ ቅረቡ፥ ስሙ፤ እናንተ ወገኖች ሆይ፥ አድምጡ፤ ምድርና ሙላዋ፥ ዓለምና ከእርስዋ የሚወጣ ሁሉ ይስሙ። |
2. | የእግዚአብሔር ቍጣ በአሕዛብ ሁሉ ላይ መዓቱም በሠራዊታቸው ሁሉ ላይ ነው፤ ፈጽሞ አጠፋቸው፥ ለመታረድም አሳልፎ ሰጣቸው። |
3. | ከእነርሱም የተገደሉት ይጣላሉ፥ የሬሳቸውም ግማት ይሸታል፥ ተራሮችም ከደማቸው የተነሣ ይርሳሉ። |
4. | የሰማይም ሠራዊት ሁሉ ይበሰብሳሉ፥ ሰማያትም እንደ መጽሐፍ ጥቅልል ይጠቀለላሉ፥ ከወይንና ከበለስም ቅጠል እንደሚረግፍ ሠራዊታቸው ሁሉ ይረግፋል። |
5. | ሰይፌ በሰማይ ሆና እስክትረካ ድረስ ጠጥታለች፤ እነሆ፥ በኤዶምያስና በረገምሁት ሕዝብ ላይ ለፍርድ ትወርዳለች። |
6. | እግዚአብሔር መሥዋዕት በባሶራ፥ ታላቅም እርድ በኤዶምያስ ምድር አለውና የእግዚአብሔር ሰይፍ በደም ተሞልታለች፥ በስብም፥ በበግ ጠቦትና በፍየል ደምም፥ በአውራም በግ ኵላሊት ስብ ወፍራለች። |
7. | ጎሽ ከእነርሱ ጋር፥ ወይፈኖችም ከኮርማዎች ጋር ይወድቃሉ፤ ምድራቸውም በደም ትረካለች፥ አፈራቸውም በስብ ትወፍራለች። |
8. | የእግዚአብሔር የበቀሉ ቀን፥ ስለ ጽዮንም ክርክር የብድራት ዓመት ነው። |
9. | የኤዶምያስም ፈሳሾች ዝፍት ሆነው ይለወጣሉ፥ አፈርዋም ዲን ይሆናል፥ መሬትዋም የሚቀጠል ዝፍት ትሆናለች። |
10. | በሌሊትና በቀንም አትጠፋም፥ ጢስዋም ለዘላለም ይወጣል፤ ከትውልድ እስከ ትውልድም ድረስ ባድማ ሆና ትኖራለች፤ ለዘላለም ዓለም ማንም አያልፍባትም። |
11. | ጭልፊትና ጃርት ግን ይወርሱአታል፤ ጕጕትና ቍራም ይኖሩባታል፤ በላይዋም የመፍረስ ገመድና የባዶነት ቱንቢ ይዘረጋባታል። |
12. | መሳፍንቶችዋን ወደ መንግሥት ይጠራሉ፥ ነገር ግን ማንም አይገኝባትም፤ አለቆችዋም ሁሉ ምናምኖች ይሆናሉ። |
13. | በአዳራሾችዋም እሾህ በቅጥሮችዋም ሳማን አሜከላ ይበቅሉባታል፤ የቀበሮም ማደሪያና የሰጐን ስፍራ ትሆናለች። |
14. | የምድረ በዳም አራዊት ከተኵሎች ጋር ይገናኛሉ፥ አጋንንትም እርስ በርሳቸው ይጠራራሉ፤ ጅንም በዚያ ትኖራለች ለእርስዋም ማረፊያ ታገኛለች። |
15. | በዚያም ዋሊያ ቤትዋን ትሠራለች እንቍላልም ትጥላለች ትቀፈቅፈውማለች ልጆችዋንም በጥላዋ ትሰበስባለች፤ በዚያም ደግሞ አሞራዎች እያንዳንዳቸው ከባልንጀሮቻቸው ጋር ይሰበሰባሉ። |
16. | በእግዚአብሔር መጽሐፍ ፈልጉ አንብቡም፤ አፌ አዝዞአልና፥ መንፈሱም ሰብስቦአቸዋልና ከእነዚህ አንዲት አትጠፋም፥ ባልንጀራውንም የሚያጣ የለም። |
17. | እርሱም ዕጣ ጣለባቸው፥ እጁም በገመድ ከፈለችላቸው፤ ለዘላለም ይገዙአታል፥ ከትውልድም እስከ ትውልድ ድረስ ይቀመጡባታል። |
← Isaiah (34/66) → |