| ← Isaiah (33/66) → |
| 1. | አንተ ሳትጠፋ የምታጠፋ፥ በአንተም ላይ ወንጀል ሳይደረግ ወንጀል የምታደርግ ወዮልህ! ማጥፋትን በተውህ ጊዜ ትጠፋለህ፤ መወንጀልንም በተውህ ጊዜ ይወነጅሉሃል። |
| 2. | አቤቱ፥ ማረን፤ አንተን ተማምነናል፤ ጥዋት ጥዋት ክንድ በመከራም ጊዜ ማዳን ሁነን። |
| 3. | ከፍጅት ድምፅ ወገኖች ሸሹ፥ በመነሣትህም አሕዛብ ተበተኑ። |
| 4. | አንበጣ እንደሚሰበስብ ምርኮአችሁ ትሰበሰባለች፥ ኩብኩባም እንደሚዘልል ሰዎች ይዘልሉበታል። |
| 5. | እግዚአብሔር በአርያም ተቀምጦአልና ከፍ ከፍ አለ፤ ጽዮንን በፍርድና በጽድቅ ሞላት። |
| 6. | የዘመንህም ጸጥታ፥ የመድኃኒት ብዛት፥ ጥበብና እውቀት ይሆናል፤ እግዚአብሔርን መፍራት መዝገቡ ነው። |
| 7. | እነሆ፥ ኃይለኞቻቸው በሜዳ ይጮኻሉ፤ የሰላም መልእክተኞች መራራ ልቅሶ ያለቅሳሉ። |
| 8. | መንገዶች ባድማ ሆኑ፥ ተላላፊም ቀረ፤ እርሱም ቃል ኪዳንን አፈረሰ ከተሞችንም ናቀ ሰውንም አልተመለከተም። |
| 9. | ምድሪቱ አለቀሰች ከሳችም፤ ሊባኖስ አፈረ ጠወለገም፤ ሳሮን እንደ ምድረ በዳ ሆነ፤ ባሳንና ቀርሜሎስ ቅጠላቸውን አረገፉ። |
| 10. | አሁን እነሣለሁ ይላል እግዚአብሔር፤ አሁን እከበራለሁ፤ አሁን ከፍ ከፍ እላለሁ። |
| 11. | ገለባን ትፀንሳላችሁ፥ እብቅንም ትወልዳላችሁ፤ እስትንፋሳችሁ የምትበላችሁ እሳት ናት። |
| 12. | አሕዛብም እንደ ተቃጠለ ኖራ፥ ተቈርጦም በእሳት እንደ ተቃጠለ እሾህ ይሆናሉ። |
| 13. | እናንተ በሩቅ ያላችሁ የሠራሁትን ስሙ፥ እናንተም በቅርብ ያላችሁ ኃይሌን እወቁ። |
| 14. | በጽዮን ያሉ ኃጢአተኞች ፈሩ፤ መንቀጥቀጥ ዝንጉዎቹን ያዘ፤ ከምትበላ እሳት ጋር መኖርን የሚችል ከእኛ ማን አለ? ለዘላለምም ከምትነድድ እሳት ጋር መኖርን የሚችል ከእኛ ማን አለ? |
| 15. | በጽድቅ የሚሄድ ቅን ነገርንም የሚናገር፥ በሽንገላ የሚገኝ ትርፍን የሚንቅ፥ መማለጃን ከመጨበጥ እጁን የሚያራግፍ፥ ደም ማፍሰስን ከመስማት ጆሮቹን የሚያደነቍር፥ ክፋትንም ከማየት ዓይኖቹን የሚጨፍን ነው። |
| 16. | እርሱ ከፍ ባለ ስፍራ ይቀመጣል፤ ጠንካራ አምባ መጠጊያው ይሆናል፤ እንጀራም ይሰጠዋል፥ ውኃውም የታመነች ትሆናለች። |
| 17. | ዓይኖችህ ንጉሥን በውበቱ ያዩታል፤ እነርሱም በሩቅ ያለች ምድርን ያዩአታል። |
| 18. | ልብህም። ጸሐፊ ወዴት አለ? መዛኝስ ወዴት አለ? ግንቦቹንስ የቈጠረ ወዴት አለ? ብሎ የሚያስፈራ ነገር ያስባል። |
| 19. | ጨካኝን ሕዝብ፥ ቋንቋው ለማስተዋል ጥልቅ የሆነውንና አንደበቱ ለማስተዋል ጸያፍ የሆነውን ሕዝብ፥ አታይም። |
| 20. | የበዓላችንን ከተማ ጽዮንን ተመልከት፤ ዓይኖችህ የሰላም ማደሪያ፥ ካስማውም ለዘላለም የማይነቀል አውታሩም ሁሉ የማይበጠስ፥ የማይወገድ ድንኳን የሆነውን ኢየሩሳሌምን ያያሉ። |
| 21. | እግዚአብሔር በዚያ የሰፉ ወንዞችና የመስኖች ስፍራ ሆኖ ከእኛ ጋር በግርማ ይሆናል፤ የሚቀዘፉ መርከቦች አይገቡባትም፥ ታላላቆችም መርከቦች አያልፉባትም። |
| 22. | እግዚአብሔር ፈራጃችን ነው፥ እግዚአብሔር ሕግን ሰጪያችን ነው፥ እግዚአብሔር ንጉሣችን ነው፤ እርሱ ያድነናል። |
| 23. | ገመዶችህ ላልተዋል፥ ደቀላቸውንም አላጸኑም፥ ሸራውንም መዘርጋት አልቻሉም። በዚያም ጊዜ የብዙ ምርኮ ብዝበዛ ተከፈለ፤ አንካሶች እንኳ ብዝበዛውን በዘበዙ። |
| 24. | በዚያም የሚቀመጥ። ታምሜአለሁ አይልም፥ በእርስዋም ለሚቀመጡ ሰዎች በደላቸው ይቅር ይባልላቸዋል። |
| ← Isaiah (33/66) → |