Isaiah (32/66)  

1. እነሆ፥ ንጉሥ በጽድቅ ይነግሣል፥ መሳፍንትም በፍርድ ይገዛሉ።
2. ሰውም ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ ከዐውሎ ነፋስም እንደ መጠጊያ፥ በጥም ቦታም እንደ ወንዝ ፈሳሽ፥ በበረሃም አገር እንደ ትልቅ ድንጋይ ጥላ ይሆናል።
3. የሚያዩትም ሰዎች ዓይኖች አይጨፈኑም፥ የሚሰሙትም ጆሮች ያደምጣሉ።
4. ጥንቃቄ የሌላቸው ሰዎች ልብ እውቀትን ታስተውላለች፥ የተብታቦችም ምላስ ደኅና አድርጋ ትናገራለች።
5. ከእንግዲህ ወዲህ ሰነፍ ከበርቴ ተብሎ አይጠራም፥ ንፉግም ለጋስ አይባልም።
6. ሰነፍ ግን ስንፍናን ይናገራል፥ ልቡም ዝንጉነትን ይፈጽም ዘንድ በእግዚአብሔርም ላይ ስሕተትን ይናገር ዘንድ የተራበችውንም ሰውነት ባዶ ያደርግ ዘንድ ከተጠማም ሰው መጠጥን ይቈርጥ ዘንድ በደልን ይሠራል።
7. የንፉግም ዕቃ ክፉ ናት፤ ችግረኛ ቅን ነገርን በተናገረ ጊዜ እንኳ እርሱ በሐሰት ቃል ድሀውን ያጠፋ ዘንድ ክፉን አሳብ ያስባል።
8. ከበርቴ ሰው ግን ለመከበር ያስባል፥ በመከበርም ጸንቶ ይኖራል።
9. እናንተ ዓለመኞች ሴቶች ሆይ፥ ተነሡ ድምፄንም ስሙ፤ እናንተ ተማምናችሁ የምትቀመጡ ሴቶች ልጆች ሆይ፥ ንግግሬን አድምጡ።
10. እናንተ ተማምናችሁ የምትቀመጡ ሴቶች ሆይ፥ ወይንን መቍረጥ ይጠፋልና፥ ፍሬም ማከማቸት አይመጣምና ከዓመትና ከጥቂት ቀን በኋላ ትንቀጠቀጣላችሁ።
11. እናንተ ዓለመኞች ሴቶች ሆይ፥ ተጠንቀቁ፤ ተማምናችሁም የምትቀመጡ ሆይ፥ ተንቀጥቀጡ፤ ልብሳችሁን አውልቁ፥ ዕራቁታችሁን ሁኑ፥ ወገባችሁንም በማቅ ታጠቁ።
12. ስለ ተወደደችውም እርሻ ስለሚያፈራውም ወይን ደረታችሁን ድቁ።
13. በሕዝቤ ምድር ላይ፥ በደስታ ከተማ ባሉት በደስታ ቤቶች ሁሉ ላይ እሾህና ኵርንችት ይወጣባቸዋል፤
14. አዳራሹ ወና ትሆናለችና፥ የብዙ ሰውም ከተማ ትለቀቃለችና፥ አምባውና ግንቡም ለዘላለም ዋሻ፥ የምድረ በዳም አህያ ደስታ፥ የመንጎችም ማሰማርያ ይሆናልና።
15. ይህም፥ መንፈስ ከላይ እስኪፈስስልን፥ ምድረ በዳውም ፍሬያማ እርሻ እስኪሆን፥ ፍሬያማውም እርሻ ዱር ተብሎ እስኪቈጠር ድረስ ይሆናል።
16. ከዚያ በኋላ ፍርድ በምድረ በዳ ይኖራል፥ ጽድቅም በፍሬያማው እርሻ ያድራል።
17. የጽድቅም ሥራ ሰላም፥ የጽድቅም ፍሬ ለዘላለም ጸጥታና መታመን ይሆናል።
18. ሕዝቤም በሰላም ማደሪያ በታመነም ቤት በጸጥተኛ ማረፊያ ይቀመጣል።
19. በረዶ ግን በዱር ላይ ይወርዳል፥ ከተማም ፈጽማ ትዋረዳለች።
20. እናንተ የበሬና የአህያ እግር እየነዳችሁ በውኃ ሁሉ አጠገብ የምትዘሩ ብፁዓን ናችሁ።

  Isaiah (32/66)