Isaiah (31/66)  

1. ስለ እርዳታ ወደ ግብጽ ለሚወርዱ በፈረሶችም ለሚደገፉ፥ ስለ ብዛታቸውም በሰረገሎች፥ እጅግ ብርቱዎችም ስለ ሆኑ በፈረሰኞች ለሚታመኑ፥ ወደ እስራኤልም ቅዱስ ለማይመለከቱ እግዚአብሔርንም ለማይፈልጉ ወዮላቸው!
2. እርሱ ግን ደግሞ ጠቢብ ነው፥ ክፉንም ነገር ያመጣል፥ ቃሉንም አይመልስም፥ በክፉም አድራጊዎች ቤት ላይ በደልንም በሚሠሩ ረዳት ላይ ይነሣል።
3. ግብጻውያን ሰዎች እንጂ አምላክ አይደሉም፥ ፈረሶቻቸውም ሥጋ እንጂ መንፈስ አይደሉም፤ እግዚአብሔርም እጁን በዘረጋ ጊዜ፥ ረጂው ይሰናከላል ተረጂውም ይወድቃል፥ ሁሉም በአንድ ላይ ይጠፋሉ።
4. እግዚአብሔርም እንዲህ ይለኛልና። አንበሳ ወይም የአንበሳ ደቦል በንጥቂያው ላይ ሲያገሳ፥ ብዙ እረኞች ቢከማቹበት ከቃላቸው እንደማይፈራ ከድምፃቸውም እንደማይዋረድ፥ እንዲሁ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በጽዮን ተራራና በኮረብታዋ ላይ ይዋጋ ዘንድ ይወርዳል።
5. እንደሚበርር ወፍ እንዲሁ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ይጋርዳታል፤ ይከልላታል፥ ይታደጋታል፥ አልፎም ያድናታል።
6. እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ አጥብቃችሁ ወደ ዐመፃችሁበት ተመለሱ።
7. በዚያም ቀን እያንዳንዳቸው እጆቻቸው ለኃጢአት የሠሩላቸውን የብሩንና የወርቁን ጣዖቶቻቸውን ይጥላሉ።
8. አሦርም የሰው ባልሆነ ሰይፍ ይወድቃል፥ የሰውም ያልሆነ ሰይፍ ይበላዋል፤ ከሰይፍም ይሸሻሉ ጐበዛዝቱም ገባሮች ይሆናሉ።
9. አምባው ከፍርሃት የተነሣ ያልፋል መሳፍንቱም ከዓላማው የተነሣ ይደነግጣሉ፥ ይላል እሳቱ በጽዮን እቶኑም በኢየሩሳሌም የሆነ እግዚአብሔር።

  Isaiah (31/66)