| ← Isaiah (3/66) → |
| 1. | እነሆ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ ድጋፍንና ብርታትን፥ የእንጀራን ድጋፍ ሁሉ የውኃውንም ድጋፍ ሁሉ፥ |
| 2. | ኃያሉንም፥ ተዋጊውንም፥ ፈራጁንም፥ ነቢዩንም፥ ምዋርተኛውንም፥ |
| 3. | ሽማግሌውንም፥ የአምሳ አለቃውንም፥ ከበርቴውንም፥ አማካሪውንም፥ ብልሁንም ሠራተኛ፥ አስማት አዋቂውንም ይነቅላል። |
| 4. | አለቆቻቸው እንዲሆኑ ብላቴኖችን አስነሣባቸዋለሁ፥ ሕፃናቶችም ይገዙአቸዋል። |
| 5. | ሕዝቡም፥ ሰው በሰው ላይ ሰውም በባልንጀራው ላይ፥ ይገፋፋል፤ ብላቴናውም በሽማግሌው ላይ የተጠቃውም በከበርቴው ላይ ይኰራል። |
| 6. | ሰውም በአባቱ ቤት ውስጥ ወንድሙን ይዞ። አንተ ልብስ አለህ አለቃም ሁንልን ይህችም ባድማ ከእጅህ በታች ትሁን ሲለው፥ |
| 7. | በዚያ ቀን ድምፁን ከፍ አድርጎ። እኔ በቤቴ ውስጥ እንጀራ ወይም ልብስ የለኝምና ባለ መድኃኒት አልሆንም፤ በሕዝቡም ላይ አለቃ አታደርጉኝም ይላል። |
| 8. | የክብሩን ዓይን ያስቈጡ ዘንድ ምላሳቸውና ሥራቸው በእግዚአብሔር ላይ ነውና ኢየሩሳሌም ተፈታች ይሁዳም ወደቀ። |
| 9. | የፊታቸውም እፍረት ይመሰክርባቸዋል፤ እንደ ሰዶምም ኃጢአታቸውን ያወራሉ፥ አይሠውሩአትም። በራሳቸው ላይ ክፉ ነገርን ሠርተዋልና ለነፍሳቸው ወዮ! |
| 10. | የሥራቸውን ፍሬ ይበላሉና ጻድቁን። መልካም ይሆንልሃል በሉት። |
| 11. | እንደ እጁ ሥራ ፍዳው ይደረግበታልና ለበደለኛ ወዮ! ክፉም ደርሶበታል። |
| 12. | ሕዝቤንስ አስገባሪዎቻቸው ይገፉአቸዋል፥ አስጨናቂዎችም ይሠለጥኑባቸዋል። ሕዝቤ ሆይ፥ የመሩአችሁ ያስቱአችኋል የምትሄዱበትንም መንገድ ያጠፋሉ። |
| 13. | እግዚአብሔር ለፍርድ ተነሥቶአል በሕዝቡም ላይ ሊፈርድ ቆሞአል። |
| 14. | እግዚአብሔር ከሕዝቡ ሽማግሌዎችና ከአለቆቻቸው ጋር ይፋረዳል፤ የወይኑን ቦታ የጨረሳችሁ እናንተ ናችሁ፤ ከድሆች የበዘበዛችሁት በቤታችሁ አለ፤ |
| 15. | ሕዝቤንም ለምን ታደቅቁአቸዋላችሁ? የድሆችንስ ፊት ለምን ትፈጫላችሁ? ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። |
| 16. | ደግሞም እግዚአብሔር እንዲህ አለ። የጽዮን ቈነጃጅት ኰርተዋልና፥ አንገታቸውንም እያሰገጉ በዓይናቸውም እያጣቀሱ፥ ፈንጠርም እያሉ፥ በእግራቸውም እያቃጨሉ ይሄዳሉና |
| 17. | ስለዚህ ጌታ የጽዮንን ቈነጃጅት አናት በቡሀነት ይመታል፥ እግዚአብሔርም ኀፍረተ ሥጋቸውን ይገልጣል። |
| 18. | በዚያም ቀን ጌታ የእግር አልቦውን ክብር፥ መርበብንም፥ ጨረቃ የሚመስለውንም ጌጥ፥ የጆሮ እንጥልጥሉንም፥ |
| 19. | አንባሩንም፥ መሸፈኛውንም፥ ቀጸላውንም፥ |
| 20. | ሰንሰለቱንም፥ መቀነቱንም፥ የሽቱውንም ዕቃ፥ |
| 21. | አሸንክታቡንም፥ የእጅና የአፍንጫ ቀለበቱንም፥ |
| 22. | የዓመት በዓልንም ልብስ፥ መጐናጸፊያውንም፥ ልግምበገላውንም፥ ከረጢቱንም፥ |
| 23. | መስተዋቱንም፥ ከጥሩ በፍታ የተሰራውንም ልብስ፥ ራስ ማሰሪያውንም፥ ዓይነ ርግቡንም ያስወግዳል። |
| 24. | እንዲህም ይሆናል፤ በሽቱ ፋንታ ግማት፥ በመታጠቂያውም ፋንታ ገመድ፥ ጠጕርንም በመንቀስ ፋንታ ቡሀነት፥ በመጐናጸፊያ ፋንታ ማቅ፥ በውበትም ፋንታ ጠባሳ ይሆናል። |
| 25. | ጕልማሶችሽ በሰይፍ፥ ኃያላንሽም በውጊያ ይወድቃሉ። |
| 26. | በሮችዋ ያዝናሉ ያለቅሱማል፤ እርስዋም ብቻዋን በምድር ላይ ትቀመጣለች። |
| ← Isaiah (3/66) → |