← Isaiah (27/66) → |
1. | በዚያም ቀን እግዚአብሔር ፈጣኑን እባብ ሌዋታንን ጠማማውንም እባብ ሌዋታንን በጠንካራ በታላቅም በብርቱም ሰይፍ ይቀጣል፥ በባሕርም ውስጥ ያለውን ዘንዶ ይገድላል። |
2. | በዚያም ቀን ለተወደደው የወይን ቦታ ተቀኙለት። |
3. | እኔ እግዚአብሔር ጠባቂው ነኝ፤ ሁልጊዜ አጠጣዋለሁ፤ ማንም እንዳይጐዳው በሌሊትና በቀን እጠብቀዋለሁ። |
4. | አልቈጣም፤ እሾህና ኵርንችት በእኔ ላይ ምነው በሰልፍ በነበሩ! በእነርሱ ላይ ተራምጄ በአንድነት ባቃጠልኋቸው ነበር። |
5. | ወይም ጕልበቴን ይያዝ፥ ከእኔ ጋር ሰላም ያድርግ፤ ከእኔ ጋር ሰላም ያድርግ። |
6. | በሚመጣው ዘመን ያዕቆብ ሥር ይሰድዳል፥ እስራኤልም ያብባል ይጨበጭብማል፤ በፍሬያቸውም የዓለሙን ፊት ይሞላሉ። |
7. | በውኑ የመቱትን እንደ መታ እንዲሁ እርሱን መታውን? ወይስ እነርሱ እንደ ተገደሉበት መገደል እርሱ ተገድሎአልን? |
8. | ነዳቸው ሰደዳቸው ቀሠፋቸው፤ የምሥራቅ ነፋስ እንደሚነፍስበት ቀን በጠንካራ ዐውሎ አስወገዳቸው። |
9. | ስለዚህም የማምለኪያ ዐፀዶችና የፀሐይ ምስሎች ዳግመኛ እንዳይነሡ የመሠዊያውን ድንጋይ ሁሉ እንደ ደቀቀ እንደ ኖራ ድንጋይ ባደረገ ጊዜ፥ እንዲሁ የያዕቆብ በደል ይሰረያል፥ ይህም ኀጢአትን የማስወገድ ፍሬ ሁሉ ነው። |
10. | የተመሸገችው ከተማ ብቻዋን ሆነች፤ እንደ ምድረ በዳ ሆና የተፈታችና የተተወች መኖሪያ ናት፤ በዚያም ጥጃ ይሰማራል በዚያም ይተኛል ቅርንጫፍዋንም ይበላል። |
11. | ጫፎችዋ በደረቁ ጊዜ ይሰበራሉ፥ ሴቶችም መጥተው ያቃጥሉአቸዋል፤ የማያስተውል ሕዝብ ነውና ስለዚህ ፈጣሪው አይራራለትም ሠሪውም ምሕረት አያደርግለትም። |
12. | በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ እግዚአብሔር ከወንዝ ፈሳሽ ጀምሮ እስከ ግብጽ ወንዝ ድረስ እህሉን ይወቃል፥ እናንተም የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ አንድ በአንድ ትሰበሰባላችሁ። |
13. | በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ታላቅ መለከት ይነፋል፥ በአሦርም የጠፉ፥ በግብጽ ምድርም የተሰደዱ ይመጣሉ፥ በተቀደሰውም ተራራ በኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር ይሰግዳሉ። |
← Isaiah (27/66) → |