← Isaiah (24/66) → |
1. | እነሆ፥ እግዚአብሔር ምድርን ባዶ ያደርጋታል፥ ባድማም ያደርጋታል፥ ይገለብጣትማል፥ በእርስዋም የተቀመጡትን ይበትናል። |
2. | እንደ ሕዝቡም እንዲሁ ካህኑ፥ እንደ ባሪያውም እንዲሁ ጌታው፥ እንደ ባሪያይቱም እንዲሁ እመቤትዋ፥ እንደሚገዛም እንዲሁ የሚሸጠው፥ እንደ አበዳሪውም እንዲሁ ተበዳሪው፥ እንደ ዕዳ አስከፋዩም እንዲሁ ዕዳ ከፋዩ ይሆናል። |
3. | ምድር መፈታትን ትፈታለች፥ ፈጽማም ትበላሻላች፤ እግዚአብሔር ይህን ቃል ተናግሮአልና። |
4. | ምድርም አለቀሰች ረገፈችም፤ ዓለም ደከመች ረገፈችም፤ የምድርም ሕዝብ ታላላቆች ደከሙ። |
5. | ምድርም ከሚቀመጡባት በታች ረክሳለች፥ ሕጉን ተላልፈዋልና፥ ሥርዓቱንም ለውጠዋልና፥ የዘላለሙንም ቃል ኪዳን አፍርሰዋልና። |
6. | ስለዚህ መርገም ምድርን ትበላለች በእርስዋም የተቀመጡ ይቀጣሉ፤ ስለዚህ የምድር ሰዎች ይቃጠላሉ ጥቂት ሰዎችም ይቀራሉ። |
7. | የወይን ጠጅ አለቀሰች፥ የወይን ንግድ ደከመች፥ ልባቸው ደስ ያለው ሁሉ ተከዙ። |
8. | የከበሮው ሐሤት ቀርቶአል፥ የደስተኞች ድምፅ ዝም ብሎአል፥ የመሰንቆ ደስታ ቀርቶአል። |
9. | እየዘፈኑም የወይን ጠጅን አይጠጡትም፥ የሚያሰክርም መጠጥ ለሚጠጡት መራራ ይሆናል። |
10. | ባድማ የሆነችው ከተማ ፈረሰች፤ ቤት ሁሉ ማንም እንዳይገባበት ተዘጋ። |
11. | ስለ ወይኑም ጠጅ በአደባባይ ጩኸት ይሆናል፤ ደስታ ሁሉ ጨልሞአል፥ የምድርም ሐሤት ፈርሶአል። |
12. | ከተማይቱም ባድማ ሆናለች፥ በርዋም በጥፋት ተመትቶአል። |
13. | የወይራን ዛፍ እንደ መምታት፥ ከወይንም መከር በኋላ ቃርሚያውን እንደ መልቀም፥ እንዲሁ በምድር መካከል በአሕዛብም መካከል ይሆናል። |
14. | እነዚህ ድምፃቸውን ያነሣሉ፥ እልልም ይላሉ፥ ስለ እግዚአብሔር ክብርም ከባሕር ይጣራሉ። |
15. | ስለዚህ እግዚአብሔርን በምሥራቅ፥ የእስራኤልንም አምላክ የእግዚአብሔርንም ስም በባሕር ደሴቶች አክብሩ። |
16. | ለጻድቁ ክብር ይሁን የሚለውን ዝማሬ ከምድር ዳርቻ ሰምተናል። እኔ ግን። ከሳሁ፥ ከሳሁ፥ ወዮልኝ! ወንጀለኞች ወንጅለዋል፤ ወንጀለኞች እጅግ ወንጅለዋል አልሁ። |
17. | በምድር ላይ የምትኖር ሆይ፥ ፍርሃትና ገደል ወጥመድም በአንተ ላይ አሉ። |
18. | የሰማይ መስኮቶች ተከፍተዋልና፥ የምድርም መሠረት ተናውጣለችና ከፍርሃት ድምፅ የሸሸ በገደል ይወድቃል፥ ከገደልም የወጣ በወጥመድ ይያዛል። |
19. | ምድር ተሰባበረች፥ ምድር ፈጽማ ደቀቀች፥ ምድር ተነዋወጠች። |
20. | ምድር እንደ ሰካር ሰው ትንገዳገዳለች፥ እንደ ዳስም ትወዛወዛለች፤ መተላለፍዋ ይከብድባታል፥ ትወድቅማለች ደግማም አትነሣም። |
21. | በዚያም ቀን እንደዚህ ይሆናል፤ እግዚአብሔር በከፍታ ያለውን ሠራዊት በከፍታ ላይ፥ በምድርም ያሉትን ነገሥታት በምድር ላይ ይቀጣቸዋል። |
22. | ግዞተኞች በጕድጓድ እንደሚከማቹ በአንድነት ይከማቻሉ፥ በግዞት ቤትም ውስጥ ተዘግተው ይኖራሉ፥ ከብዙ ቀንም በኋላ ይጐበኛሉ። |
23. | የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም ላይ ይነግሣልና፥ በሽማግሌዎቹም ፊት ክብር ይሆናልና ጨረቃ ይታወካል ፀሐይም ያፍራል። |
← Isaiah (24/66) → |