| ← Isaiah (23/66) → |
| 1. | ስለ ጢሮስ የተነገረ ሸክም። የተርሴስ መርከቦች ሆይ፥ አልቅሱ፤ ፈርሶአልና ቤት የለም፥ መግባትም የለም፤ ከኪቲም አገር ጀምሮ ተገልጦላቸዋል። |
| 2. | እናንተ በደሴት የምትኖሩ በባሕርም የምትሻገሩ የሲዶና ነጋዴዎች ንግድ የሞሉባችሁ ሆይ፥ ጸጥ በሉ። |
| 3. | የሺሖር ዘርና የዓባይ ወንዝ መከር በብዙ ውኆች ላይ ገቢዋ ነበረ፤ እርስዋም የአሕዛብ መናገጃ ነበረች። |
| 4. | ሲዶና ሆይ፥ ባሕር፥ የባሕር ምሽግ። አላማጥሁም፥ አልወለድሁም፤ ጐበዛዝትንም አላሳደግሁም፥ ደናግልንም አላሳደግሁም ብሎ ተናግሮአልና እፈሪ። |
| 5. | ወሬዋ ወደ ግብጽ በደረሰ ጊዜ በጢሮስ ወሬ ምጥ ይይዛቸዋል። |
| 6. | ወደ ተርሴስ ተሻገሩ፤ እናንተ በደሴት የምትኖሩ አልቅሱ። |
| 7. | በቀድሞ ዘመን ተመሥርታ የነበረችው፥ በዚያም እንደ እንግዳ ሆና ትኖር ዘንድ እግሮችዋ ወደ ሩቅ ያፈለሱአት የደስታችሁ ከተማ ይህች ናትን? |
| 8. | አክሊል ባስጫነች ከተማ በጢሮስ ላይ ይህን የወሰነ ማን ነው? ነጋዴዎችዋ አለቆች ናቸው፥ በእርስዋም የሚሸጡና የሚለውጡ የምድር ክቡራን ናቸው። |
| 9. | የክብርን ሁሉ ትዕቢት ይሽር ዘንድ የምድርንም ክቡራን ሁሉ ያስንቅ ዘንድ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ወስኖታል። |
| 10. | የተርሴስ ልጅ ሆይ፥ የሚከለክልሽ የለምና እንደ ዓባይ ወንዝ በአገርሽ ላይ ጐርፈሽ እለፊ። |
| 11. | በባሕር ላይ እጁን ዘረጋ መንግሥታትንም አናወጠ፤ ምሽጎችዋንም ያጠፉ ዘንድ እግዚአብሔር ስለ ከነዓን አገር አዘዘ። |
| 12. | እርሱም። አንቺ የተበደልሽ የሲዶና ድንግል ልጅ ሆይ፥ ከእንግዲህ ወዲህ ደስ አይበልሽ፤ ተነሥተሽ ወደ ኪቲም ተሻገሪ፥ በዚያም ደግሞ አታርፊም አለ። |
| 13. | እነሆ፥ የከለዳውያን አገር! ይህ ሕዝብ ሆኖ አይገኝም፤ አሦራውያን ለምድረ በዳ አራዊት ሰጥተውታል፤ ግንቦቻቸውን ሠሩ፥ አዳራሾችዋንም አፈረሱ፥ ባድማም አደረጓት። |
| 14. | እናንተ የተርሴስ መርከቦች ሆይ፥ ምሽጋችሁ ፈርሶአልና ዋይ በሉ። |
| 15. | በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ጢሮስ እንደ አንድ ንጉሥ ዘመን ሰባ ዓመት ያህል የተረሳች ትሆናለች፤ ከሰባ ዓመት በኋላ ግን ለጢሮስ በጋለሞታ ዘፈን እንደሚሆን እንዲሁ ይሆናል። |
| 16. | አንቺ የተረሳሽ ጋለሞታ ሆይ፥ መሰንቆ ያዢ በከተማ ላይም ዙሪ፤ መታሰቢያም ይሆንልሽ ዘንድ ዜማን አሳምሪ ዘፈንሽንም አብዢ። |
| 17. | ከሰባ ዓመትም በኋላ እግዚአብሔር ጢሮስን ይጐበኛታል፥ ወደ ዋጋዋም ትምለሳለች፥ ደግሞም በምድር ፊት ላይ ከሆኑ ከዓለም መንግሥታት ሁሉ ጋር ትገለሙታለች። |
| 18. | ንግድዋና ዋጋዋ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሆናል፤ ንግድዋም በልተው ይጠግቡ ዘንድ ማለፊያም ልብስ ይለብሱ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ለሚኖሩ ይሆናል እንጂ በዕቃ ቤትና በግምጃ ቤት ውስጥ አይከተትም። |
| ← Isaiah (23/66) → |