| ← Isaiah (21/66) → |
| 1. | በባሕር አጠገብ ስላለው ስለ ምድረ በዳ የተነገረ ሸክም። ዐውሎ ነፋስ ከደቡብ እንደሚወጣ፥ እንዲሁ ከሚያስፈራ አገር ከምድረ በዳ ይወጣል። |
| 2. | ከባድ ራእይ ተነገረኝ፤ ወንጀለኛው ይወነጅላል አጥፊውም ያጠፋል። ኤላም ሆይ፥ ውጪ፤ ሜዶን ሆይ፥ ክበቢ፤ ትካዜውን ሁሉ አስቀርቻለሁ። |
| 3. | ስለዚህ ወገቤ ሕመም ተሞላ፤ እንደምትወልድ ሴት ምጥ ያዘኝ፤ ከሕመሜ የተነሣ አልሰማም፥ ከድንጋጤም የተነሣ አላይም። |
| 4. | ልቤ ተንበደበደ፥ ድንጋጤ አስፈራኝ፥ ተስፋ ያደረግሁትም ድንግዝግዝታ መንቀጥቀጥ ሆነብኝ። |
| 5. | ማዕዱን ያዘጋጃሉ፥ ምንጣፉንም ይዘረጋሉ፥ ይበሉማል፥ ይጠጡማል፤ እናንተ መሳፍንት ሆይ፥ ተነሡ፥ ጋሻውን አዘጋጁ። |
| 6. | ጌታ እንዲህ ብሎኛልና። ሂድ ጉበኛም አቁም፥ የሚያየውንም ይናገር። |
| 7. | በከብት የሚቀመጡትን፥ ሁለት ሁለት እየሆኑ የሚሄዱት ፈረሰኞች፥ በአህዮች የሚቀመጡትንና በግመሎች የሚቀመጡትን ባየ ጊዜ በጽኑ ትጋት አስተውሎ ተግቶም ያድምጥ። |
| 8. | ያየውም። ጌታ ሆይ፥ ቀኑን ሁሉ ዘወትር በማማ ላይ ቆሜአለሁ፥ ሌሊቱንም ሁሉ በመጠበቂያዬ ላይ ተተክያለሁ፥ |
| 9. | እነሆም፥ በፈረሶች የሚቀመጡ፥ ሁለት ሁለት ሁነው የሚሄዱ ፈረሰኞች ይመጣሉ ብሎ ጮኸ፤ እርሱም መልሶ። ባቢሎን ወደቀች ወደቀች፥ የተቀረጹም የአማልክቶችዋ ምስሎች ሁሉ በምድር ላይ ተጥለው ደቀቁ አለ። |
| 10. | እናንተ በአውድማዬ ላይ የተወቃችሁ የአውድማዬ ልጆች ሆይ፥ ከእስራኤል አምላክ ከሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሰማሁትን ነገርኋችሁ። |
| 11. | ስለ ኤዶምያስ የተነገረ ሸክም። አንዱ ከሴይር። ጕበኛ ሆይ፥ ሌሊቱ ምን ያህል ነው? ጕበኛ ሆይ፥ ሌሊቱ ምን ያህል ነው? ብሎ ጠራኝ። |
| 12. | ጕበኛውም። ይነጋል ድግሞም ይመሻል፤ ትጠይቁ ዘንድ ብትወድዱ ጠይቁ፤ ተመልሳችሁም ኑ አለ። |
| 13. | ስለ ዓረብ የተነገረ ሸክም። የድዳናውያን ነጋዴዎች ሆይ፥ በዓረብ ዱር ውስጥ ታድራላችሁ። |
| 14. | በቴማን የምትኖሩ ሆይ፥ ወደ ተጠሙት ሰዎች ውኃ አምጡ እንጀራ ይዛችሁ የሸሹትን ሰዎች ተቀበሉአቸው። |
| 15. | ከሰይፍ፥ ከተመዘዘው ሰይፍ፥ ከተለጠጠውም ቀስት ከጽኑም ሰልፍ ሸሽተዋልና። |
| 16. | ጌታ እንዲህ ብሎኛልና። እንደ ምንደኛ ዓመት በአንድ ዓመት ውስጥ የቄዳር ክብር ሁሉ ይጠፋል፤ |
| 17. | ከቀስተኞች ቍጥር የቀሩት፥ የቄዳር ልጆች ኃያላን፥ ያንሳሉ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ተናግሮአልና። |
| ← Isaiah (21/66) → |