Isaiah (20/66)  

1. የአሦር ንጉሥ ሳርጎን ተርታንን በሰደደ ጊዜ እርሱም ወደ አዛጦን በመጣ ጊዜ አዛጦንም ወግቶ በያዛት ጊዜ፥
2. በዚያ ዓመት እግዚአብሔር የአሞጽን ልጅ ኢሳይያስን። ሂድ፥ ማቅህን ከወገብህ አውጣ ጫማህንም ከእግርህ አውልቅ ብሎ ተናገረው። እንዲህም አደረገ፥ ራቁቱንም ባዶ እግሩንም ሄደ።
3. እግዚአብሔርም አለ። ባሪያዬ ኢሳይያስ በግብጽና በኢትዮጵያ ላይ ሦስት ዓመት ለምልክትና ለተአምራት ሊሆን ራቁቱንና ባዶ እግሩን እንደ ሄደ፥
4. እንዲሁ የአሦር ንጉሥ የግብጽንና የኢትዮጵያን ምርኮ፥ ጐበዛዝቱንና ሽማግሌዎቹን፥ ራቁታቸውንና ባዶ እግራቸውን አድርጎ ገላቸውንም ገልጦ፥ ለግብጽ ጕስቍልና ይነዳቸዋል።
5. እነርሱም ከተስፋቸው ከኢትዮጵያ ከትምክሕታቸውም ከግብጽ የተነሣ ይፈራሉ ያፍሩማል፤
6. በዚያም ቀን በዚች ባሕር ዳርቻ የሚቀመጡ። እነሆ፥ ከአሦር ንጉሥ እንድን ዘንድ ለእርዳታ ወደ እነርሱ የሸሸንበት ተስፋችን ይህ ነበረ፤ እኛስ እንዴት እናመልጣለን? ይላሉ።

  Isaiah (20/66)