← Isaiah (2/66) → |
1. | የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው ቃል። |
2. | በዘመኑም ፍጻሜ የእግዚአብሔር ቤት ተራራ በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ ይቆማል፥ ከኮረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፥ አሕዛብም ሁሉ ወደ እርሱ ይሰበሰባሉ። |
3. | ሕግ ከጽዮን የእግዚአብሔርም ቃል ከኢየሩሳሌም ይወጣልና ብዙዎች አሕዛብ ሄደው። ኑ፥ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፥ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፥ በጎዳናውም እንሄዳለን ይላሉ። |
4. | በአሕዛብም መካከል ይፈርዳል፥ በብዙ አሕዛብም ላይ ይበይናል፤ ሰይፋቸውንም ማረሻ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፥ ሰልፍም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም። |
5. | እናንተ የያዕቆብ ቤት ሆይ፥ ኑ፥ በእግዚአብሔር ብርሃን እንሂድ። |
6. | ሕዝብህን የያዕቆብን ቤት ትተሃልና፤ ይኸውም የምሥራቅን ሰዎች አመል ስለ ተሞሉ፥ እንደ ፍልስጥኤማውያንም ምዋርተኞች ስለ ሆኑ፥ ከባዕድ ልጆችም ጋር ስለ ተባበሩ ነው። |
7. | ምድራቸው በብርና በወርቅ ተሞልታለች፥ ለመዛግብቶቻቸውም ፍጻሜ የለውም፤ ምድራቸውም ደግሞ በፈረሶች ተሞልታለች፥ ለሠረገሎቻቸውም ፍጻሜ የለውም። |
8. | ምድራቸው ደግሞ በጣዖታት ተሞልታለች፤ ጣቶቻቸውም ላደረጉት ለእጃቸው ሥራ ይሰግዳሉ። |
9. | ታናሹም ሰው ዝቅ ብሎአል፥ ጨዋውም ተዋርዶአል፤ ኃጢአታቸውንም ይቅር አትበላቸው። |
10. | ከእግዚአብሔር ማስደንገጥና ከግርማው ክብር የተነሣ ወደ ድንጋይ ዋሻ ግባ፥ በመሬትም ውስጥ ተሸሸግ። |
11. | ከፍ ያለችውም የሰው ዓይን ትዋረዳለች፥ የሰዎችም ኵራት ትወድቃለች፥ በዚያም ቀን እግዚአብሔር ብቻውን ከፍ ከፍ ይላል። |
12. | የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቀን በትዕቢተኛውና በኵራተኛው ሁሉ ላይ ከፍ ባለውም ላይ ይሆናል፥ እርሱም ይዋረዳል፤ |
13. | ደግሞም በረጅሙ ከፍ ባለው በሊባኖስ ዝግባ ሁሉ ላይ፥ በባሳንም ዛፍ ሁሉ ላይ፥ |
14. | በረጅሙም ተራራ ሁሉ ላይ፥ ከፍ ባለውም ኮረብታ ሁሉ ላይ፥ |
15. | በረጅሙም ግንብ ሁሉ ላይ፥ በተመሸገውም ቅጥር ሁሉ ላይ፥ |
16. | በተርሴስም መርከብ ሁሉ ላይ፥ በሚያማምሩ ጣዖታትም ሁሉ ላይ ይሆናል። |
17. | ሰውም ሁሉ ይዋረዳል፥ የሰውም ኵራት ይወድቃል፥ በዚያም ቀን እግዚአብሔር ብቻ ከፍ ከፍ ይላል። |
18. | ጣዖቶቻቸውም ሁሉ ፈጽመው ይጠፋሉ። |
19. | እግዚአብሔርም ምድርን ያናውጥ ዘንድ በተነሣ ጊዜ ሰዎች ከማስደንገጡና ከግርማው ክብሩ የተነሣ ወደ ድንጋይ ዋሻና ወደ ምድር ንቃቃት ውስጥ ይገባሉ። |
20. | በዚያን ቀን ሰው ይሰግድላቸው ዘንድ ያበጁአቸውን የብሩንና የወርቁን ጣዖቶቹን ለፍልፈልና ለሌሊት ወፍ ይጥላል። |
21. | እግዚአብሔርም ምድርን ያናውጥ ዘንድ በተነሣ ጊዜ ከማስደንገጡና ከግርማው ክብር የተነሣ ወደ ድንጋይ ዋሻና ወደ ተሰነጠቁ ዓለቶች ውስጥ ይገባሉ። |
22. | እስትንፋሱ በአፍንጫው ውስጥ ያለበትን ሰው ተዉት፤ እርሱ ስለ ምን ይቈጠራል? |
← Isaiah (2/66) → |