| ← Isaiah (19/66) → |
| 1. | ስለ ግብጽ የተነገረ ሸክም። እነሆ፥ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና እይበረረ ወደ ግብጽ ይመጣል፤ የግብጽም ጣዖታት በፊቱ ይርዳሉ፥ የግብጽም ልብ በውስጥዋ ይቀልጣል። |
| 2. | ግብጻውያንን በግብጻውያን ላይ አስነሣለሁ፤ ወንድምም ወንድሙን፥ ሰውም ባልንጀራውን፥ ከተማም ከተማን፥ መንግሥትም መንግሥትን ይወጋል። |
| 3. | የግብጽም መንፈስ በውስጥዋ ባዶ ይሆናል፥ ምክራቸውንም አጠፋለሁ፤ እነርሱም ጣዖቶቻቸውን በድግምት የሚጠነቍሉትንም መናፍስት ጠሪዎቻቸውንም ጠንቋዮቻቸውንም ይጠይቃሉ። |
| 4. | ግብጻውያንንም በጨካኝ ጌታ እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ ጨካኝ ንጉሥም ይገዛቸዋል ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። |
| 5. | ውኆችም ከባሕር ይደርቃሉ፥ ወንዙም ያንሳል ደረቅም ይሆናል። |
| 6. | ወንዞቹም ይገማሉ፥ የግብጽም መስኖች ያንሳሉ ይደርቃሉም፤ ደንገልና ቄጤማ ይጠወልጋሉ። |
| 7. | በዓባይ ወንዝ ዳር ያለው መስክ በዓባይም ወንዝ አጠገብ የተዘራ እርሻ ሁሉ ይደርቃል፥ ይበተንማል፥ አይገኝምም። |
| 8. | ዓሣ አጥማጆቹ ያዝናሉ፥ በዓባይም ወንዝ መቃጥን የሚጥሉት ሁሉ ያለቅሳሉ፥ በውኆችም ላይ መረብ የሚዘረጉት ይዝላሉ። |
| 9. | የተበጠረውንም የተልባ እግር የሚሠሩ፥ ነጩንም ልብስ የሚሠሩ ሸማኔዎች ያፍራሉ። |
| 10. | ደገፋዎችዋም ሁሉ ይሰባበራሉ፥ የደመወዘኞችም ነፍስ ትተክዛለች። |
| 11. | የጣኔዎስ አለቆች ፍጹም ሰነፎች ናቸው፤ ፈርዖንን የሚመክሩ ጥበበኞች ምክራቸው ድንቍርና ሆነች። ፈርዖንን። እኛ የጥበበኞች ልጆች የቀደሙም ነገሥታት ልጆች ነን እንዴት ትሉታላችሁ? |
| 12. | አሁንሳ ጥበበኞችህ የት አሉ? አሁን ይንገሩህ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በግብጽ ላይ ያሰበውን ይወቁ። |
| 13. | የጣኔዎስ አለቆች ሰነፎች ሆነዋል፥ የሜምፎስም አለቆች ተሸንግለዋል፤ የነገዶችዋ የማዕዘን ድንጋዮች የሆኑ ግብጽን አሳቱ። |
| 14. | እግዚአብሔር የጠማምነትን መንፈስ በውስጥዋ ደባልቆአል፤ ሰካር በትፋቱ እንዲስት እንዲሁ ግብጽን በሥራዋ ሁሉ አሳቱ። |
| 15. | ራስ ወይም ጅራት የሰሌን ቅርንጫፍ ወይም እንግጫ ቢሆን ሊሠራ የሚችል ሥራ ለግብጽ አይሆንላትም። |
| 16. | በዚያ ቀን ግብጻውያን እንደ ሴቶች ይሆናሉ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ ከሚያንቀሳቅሳት ከእጁ መንቀሳቀስ የተነሣ ይሸበራሉ ይፈሩማል። |
| 17. | የይሁዳም ምድር ግብጽን የምታስደነግጥ ትሆናለች፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከመከረባት ምክር የተነሣ ወሬዋን የሚሰማ ሁሉ ይፈራል። |
| 18. | በዚያ ቀን በግብጽ ምድር በከነዓን ቋንቋ የሚናገሩ፥ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔርም የሚምሉ አምስት ከተሞች ይሆናሉ፤ ከነዚህም አንዲቱ የጥፋት ከተማ ተብላ ትጠራለች። |
| 19. | በዚያ ቀን በግብጽ ምድር መካከል ለእግዚአብሔር መሠዊያ፥ በዳርቻዋም ለእግዚአብሔር ዓምድ ይሆናል። |
| 20. | ይህም ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር በግብጽ ምድር ምልክትና ምስክር ይሆናል፤ ከሚያስጨንቁአቸው የተነሣ ወደ እግዚአብሔር ይጮኻሉና፥ እርሱም መድኃኒትንና ኃያልን ሰድዶ ያድናቸዋልና። |
| 21. | በዚያም ቀን እግዚአብሔር በግብጽ የታወቀ ይሆናል፥ ግብጽAውያንም እግዚአብሔርን ያውቃሉ፤ በመሥዋዕትና በቍርባን ያመልካሉ፥ ለእግዚአብሔርም ስእለት ይሳላሉ ይፈጽሙትማል። |
| 22. | እግዚአብሔርም ግብጽን ይመታታል፤ ይመታታል ይፈውሳታልም፤ ወደ እግዚአብሔርም ይመለሳሉ እርሱም ይለመናቸዋል ይፈውሳቸውማል። |
| 23. | በዚያ ቀን ከግብጽ ወደ አሦር መንገድ ይሆናል፥ አሦራዊውም ወደ ግብጽ፥ ግብጻዊውም ወደ አሦር ይገባል፤ ግብጻውያንም ከአሦራውያን ጋር ይሰግዳሉ። |
| 25. | የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። ሕዝቤ ግብጽ፥ የእጄም ሥራ አሦር፥ ርስቴም እስራኤል የተባረከ ይሁን ብሎ ይባርካቸዋልና በዚያ ቀን እስራኤል ለግብጽና ለአሦር ሦስተኛ ይሆናል፥ በምድርም መካከል በረከት ይሆናል። |
| ← Isaiah (19/66) → |