Isaiah (17/66)  

1. ስለ ደማስቆ የተነገረ ሸክም። እነሆ፥ ደማስቆ ከተማ ከመሆን ተቋርጣለች፤ ባድማና የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች።
2. ከተሞችዋ ለዘላለም የተፈቱ ይሆናሉ፤ ለመንጋ ማሰማሪያ ሆናሉ፤ መንጎች በዚያ ያርፋሉ የሚያስፈራቸውም የለም።
3. ምሽግም ከኤፍሬም፥ መንግሥትም ከደማስቆ ተወገደች፤ የሶርያም ቅሬታ እንደ እስራኤል ልጆች ክብር ይሆናል ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
4. በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ የያዕቆብ ክብር ይደክማል የሥጋውም ውፍረት ይከሳል።
5. አጫጅ የቆመውን እህል በእጁ ሰብስቦ ዛላውን እንደሚያጭድ ይሆናል፤ በራፋይም ሸለቆ ቃርሚያ እንደሚለቅም እንዲሁ ይሆናል።
6. ወይራ በተመታ ጊዜ ሁለት ወይም ሦስት ፍሬ በራሱ ላይ እንደሚቀር፥ አራት ወይም አምስት በዛፊቱ ጫፍ እንደሚገኝ፥ በእርሱ ዘንድ ቃርሚያ ይቀራል ይላል የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር።
7. በዚያ ቀን ሰው ወደ ፈጣሪው ይመለከታል፥ ዓይኖቹም ወደ እስራኤል ቅዱስ ያያሉ።
8. እጁም የሠራችውን መሠዊያ አይመለከትም፤ ጣቶቹም ወደ አበጁአቸው፥ ወደ ማምለኪያ ዐፀዶች ወይም ወደ ፀሐይ ምስሎች፥ አያይም።
9. በዚያም ቀን በእስራኤል ልጆች ፊት የአሞራውያንና የኤውያውያን ከተሞች እንደ ተፈቱ፥ እንዲሁ ከተሞችህ ይፈታሉ፥ ባድማም ይሆናሉ።
10. የደኅንነትህን አምላክ ረስተሃል፥ የረድኤትህንም ጌታ አላሰብህም፤ ስለዚህ ያማረውን ተክል ተክለሃል፥ እንግዳንም ዘር ዘርተሃል።
11. በተከልህበት ቀን ታበቅለዋለህ፥ በነጋውም ዘርህን እንዲያብብ ታደርገዋለህ፤ ነገር ግን በኀዘንና በትካዜ ቀን መከሩ ይሸሻል።
12. እንደ ባሕር ሞገድ ድምፅ ለሚተምሙ ለወገኖች ብዛት፥ እንደ ኃይለኛም ውኃ ጩኸት ለሚጮኹ አሕዛብ ወዮላቸው!
13. አሕዛብ እንደ ብዙ ውኃ ጩኸት ይጮኻሉ፤ እርሱ ግን ይገሥጻቸዋል፥ እነርሱም እየሸሹ ይርቃሉ፥ በተራራም ላይ እንዳለ እብቅ በነፋስ ፊት፥ ዐውሎ ነፋስ እንደሚያዞረው ትቢያ ይበተናሉ።
14. በመሸ ጊዜ፥ እነሆ፥ ድንጋጤ አለ፤ ከማለዳም በፊት አይገኙም። የዘረፉን ሰዎች እድል ፈንታ፥ የበዘበዙን ዕጣ ይህ ነው።

  Isaiah (17/66)