Isaiah (15/66)  

1. ስለ ሞዓብ የተነገረ ሸክም። የሞዓብ ዔር በሌሊት ፈርሶ ጠፋ፤ ቂር የሚባልም የሞዓብ ምሽግ በሌሊት ፈርሶ ጠፋ።
2. ወደ ባይት ወደ ዲቦንም ወደ ኮረብታ መስገጃዎችም ለልቅሶ ወጥተዋል፤ ሞዓብ በናባው በሜድባ ላይ ታለቅሳለች፤ ራሳቸው ሁሉ ተነጭቶአል፥ ጢማቸውም ሁሉ ተላጭቶአል።
3. በየመገዳቸውም በማቅ ታጥቀዋል፤ በየሰገነቶቻቸውና በየአደባባዮቻቸው እንባ እጅግ እያፈሰሱ ሁሉም አልቅሰዋል።
4. ሐሴቦንና ኤልያሊ ጮኹ፤ ድምፃቸው እስከ ያሀጽ ድረስ ይሰማል፤ ስለዚህ የሞዓብ ሰልፈኞች ጮኹ፤ ነፍስዋ በውስጥዋ ተንቀጠቀጠች።
5. ልቤ ስለ ሞዓብ ጮኸ፤ ከእርስዋም የሚሸሹ ወደ ዞዓር ወደ ዔግላት ሺሊሺያ ኰበለሉ፤ በሉሒት ዓቀበት ላይ እያለቀሱ ይወጣሉ፥ በሖሮናይምም መንገድ የዋይታ ጩኸት ያነሣሉ።
6. የኔምሬም ውኆች ይደርቃሉ፤ ሣሩም ደርቋል፥ ለጋውም ጠውልጓል፥ ልምላሜውም ሁሉ የለም።
7. ስለዚህ የሰበሰቡትን ሀብትና መዝገባቸውን ወደ አኻያ ዛፍ ወንዝ ማዶ ይወስዱታል።
8. ጩኸት የሞዓብን ዳርቻ ሁሉ ዞረ፤ ልቅሶዋም ወደ ኤግላይምና ወደ ብኤርኢሊም ደረሰ።
9. የዲሞንም ውኃ ደም ተሞልታለች፤ በዲሞንም ላይ ሥቃይን እጨምራለሁ፥ ከሞዓባውያንም በሚያመልጡ፥ ከምድርም በሚቀሩ ላይ አንበሳን አመጣለሁ።

  Isaiah (15/66)