← Isaiah (13/66) → |
1. | የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ያየው ስለ ባቢሎን የተንገረ ሸክም። |
2. | ምድረ በዳ በሆነ ተራራ ላይ ምልክትን አቁሙ፥ ድምፅንም ከፍ አድርጉባቸው፤ በአለቆችም ደጆች እንዲገቡ በእጅ ጥቀሱ። |
3. | ቍጣዬን ይፈጽሙ ዘንድ ቅዱሳኔን አዝዣለሁ፥ እኔ ኃያላኔንና በታላቅነቴ ደስ የሚላቸውን ጠርቻለሁ። |
4. | በተራሮች ላይ እንደ ታላቅ ሕዝብ ድምፅ የሆነ የብዙ ሰው ድምፅ አለ። የከተማቹት የአህዛብ መንግሥታት የውካታ ጫጫታ አለ። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሠራዊትን ለሰልፍ አሰልፎአል። |
5. | እግዚአብሔርና የቍጣው የጦር ዕቃ ምድርን ሁሉ ያጠፉአት ዘንድ ከሩቅ አገር ከሰማይ ዳርቻ ይመጣሉ። |
6. | የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአልና፥ አልቅሱ፤ ሁሉን ከሚችል አምላክ ዘንድ እንደሚመጣ ጥፋት ይመጣል። |
7. | ስለዚህ እጅ ሁሉ ትዝላለች፥ የሰውም ሁሉ ልብ ይቀልጣል። |
8. | ይደነግጣሉ፤ ምጥና ሕማም ይይዛቸዋል፥ እንደምትወልድ ሴትም ያምጣሉ፤ አንዱም በሌላው ይደነቃል፥ ፊታቸውም የነበልባል ፊት ነው። |
9. | እነሆ፥ ምድሪቱን ባድማ ሊያደርግ፥ ኃጢአተኞችዋንም ከእርስዋ ዘንድ ሊያጠፋ ጨካኝ ሆኖ በመዓትና በጽኑ ቍጣ ተሞልቶ የእግዚአብሔር ቀን ይመጣል። |
10. | የሰማይም ከዋክብትና ሠራዊቱ ብርሃናቸውን አይሰጡም፥ ፀሐይም በወጣች ጊዜ ትጨልማለች፥ ጨረቃም በብርሃኑ አያበራም። |
11. | ዓለሙን ስለ ክፋታቸው ክፉዎቹንም ስለ በደላቸው እቀጣለሁ፤ የትዕቢተኞችንም ኵራት አዋርዳለሁ። |
12. | የቀሩትም ከጥሩ ወርቅ ይልቅ የከበሩ ይሆናሉ፥ ሰውም ከኦፊር ወርቅ ይልቅ የከበረ ይሆናል። |
13. | ስለዚህ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር መዓት በጽኑ ቍጣ ቀንም ሰማያትን አነቃንቃለሁ፥ ምድርም ከስፍራዋ ትናወጣለች። |
14. | እንደ ተባረረም ሚዳቋ፥ ማንም እንደማይሰበስበው እንደ በግ መንጋ፥ ሰው ሁሉ ወደ ወገኑ ይመለሳል፥ ሁሉም ወደ አገሩ ይሸሻል። |
15. | የተገኘ ሁሉ የተወጋ ይሆናል፥ የተያዘም ሁሉ በሰይፍ ይወድቃል። |
16. | ሕፃናቶቻቸውም በፊታቸው ይጨፈጨፋሉ፥ ቤቶቻቸውም ይበዘበዛሉ፥ ሚስቶቻቸውም ይነወራሉ። |
17. | እነሆ፥ ብር የማይሹትን፥ ወርቅም የማያምራቸውን ሜዶናውያንን በላያቸው አስነሣለሁ። |
18. | ፍላጾቻቸውም ጎበዞችን ይጨፈጭፋሉ፥ የማኅፀንንም ፍሬ አይምሩም፥ ዓይኖቻቸውም ለሕፃናት አይራሩም። |
19. | እግዚአብሔርም ሰዶምንና ገሞራን ባፈረሰ ጊዜ እንደ ነበረው፥ የመንግሥታት ክብር የከለዳውያንም ትዕቢት ጌጥ ባቢሎን እንዲሁ ትሆናለች። |
20. | ለዘላለም የሚቀመጥባት አይገኝም፥ ከትውልድ እስከ ትውልድ ድረስ ሰው አይኖርባትም፤ ዓረባውያንም ድንኳንን በዚያ አይተክሉም፥ እረኞችም መንጎቻቸውን በዚያ አያሳርፉም። |
21. | በዚያም የምድረ በዳ አራዊት ያርፋሉ፥ ጕጕቶችም በቤቶቻቸው ይሞላሉ፤ ሰጎኖችም በዚያ ይኖራሉ፥ በዚያም አጋንንት ይዘፍናሉ። |
22. | ተኵላዎችም በግንቦቻቸው፥ ቀበሮችም በሚያማምሩ አዳራሾቻቸው ይጮኻሉ፤ ጊዜዋም ለመምጣት ቀርቦአል ቀንዋም አይዘገይም። |
← Isaiah (13/66) → |