7. | | ላምና ድብ አብረው ይሰማራሉ፥ ግልገሎቻቸውም በአንድነት ያርፋሉ፤ አንበሳም እንደ በሬ ገለባ ይበላል። 8 የሚጠባውም ሕፃን በእባብ ጕድጓድ ላይ ይጫወታል፥ ጡት የጣለውም ሕፃን በእፉኝት ቤት ላይ እጁን ይጭናል። 9 በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ አይጐዱም አያጠፉምም፤ ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለችና። 10 በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ለአሕዛብ ምልክት ሊሆን የቆመውን የእሴይን ሥር አሕዛብ ይፈልጉታል፤ ማረፊያውም የተከበረ ይሆናል። 11 በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ የቀረውን የሕዝቡን ቅሬታ ከአሦርና ከግብጽ፥ ከጳትሮስና ከኢትዮጵያ፥ ከኤላምና ከሰናዖር ከሐማትም፥ ከባሕርም ደሴቶች ይመልስ ዘንድ ጌታ እንደ ገና እጁን ይገልጣል። 12 ለአሕዛብም ምልክትን ያቆማል፥ ከእስራኤልም የተጣሉትን ይሰበስባል፥ ከይሁዳም የተበተኑትን ከአራቱ የምድር ማዕዘኖች ያከማቻል። 13 የኤፍሬምም ምቀኝነት ይርቃል፥ ይሁዳንም የሚያስጨንቁ ይጠፋሉ፤ ኤፍሬምም በይሁዳ አይቀናም፥ ይሁዳም ኤፍሬምን አያስጨንቅም። 14 በምዕራብም በኩል በፍልስጥኤማውያን ጫንቃ ላይ እየበረሩ ይወርዳሉ፥ የምሥራቅንም ልጆች በአንድነት ይበዘብዛሉ፤ በኤዶምያስና በሞዓብም ላይ እጃቸውን ይዘረጋሉ፥ የአሞንም ልጆች ለእነርሱ ይታዘዛሉ። 15 እግዚአብሔርም የግብጽን ባሕር ያጠፋል፤ በትኩሱም ነፋስ እጁን በወንዙ ላይ ያነሣል፥ ሰባት ፈሳሾችንም አድርጎ ይመታዋል፥ ሰዎችም በጫማቸው እንዲሻገሩ ያደርጋቸዋል። 16 ከግብጽም በወጣ ጊዜ ለእስራኤል እንደ ነበረ፥ ለቀረው ለሕዝቡ ቅሬታ ከአሦር ጐዳና ይሆናል። |