Isaiah (1/66)  

1. በይሁዳ ነገሥታት በዖዝያንና በኢዮአታም በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመን ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው የአሞጽ ልጅ የኢሳይያስ ራእይ።
2. እግዚአብሔር ተናግሮአልና ሰማያት ስሙ፥ ምድርም አድምጪ፤ ልጆችን ወለድሁ አሳደግሁም፥ እነርሱም አመጹብኝ።
3. በሬ የገዢውን አህያም የጌታውን ጋጣ አወቀ፤ እስራኤል ግን አላወቀም፥ ሕዝቤም አላስተዋለም።
4. ኃጢአተኛ ወገንና በደል የተሞላበት ሕዝብ፥ የክፉዎች ዘር፥ ርኵሰትን የምታደርጉ ልጆች ሆይ፥ ወዮላችሁ! እግዚአብሔርን ትተዋል የእስራኤልንም ቅዱስ አቃልለዋል ወደ ኋላቸውም እየሄዱ ተለይተዋል።
5. ደግሞስ ዓመፃ እየጨመራችሁ ለምን ገና ትቀሰፋላችሁ? ራስ ሁሉ ለሕመም ልብም ሁሉ ለድካም ሆኗል።
6. ከእግር ጫማ አንስቶ እስከ ራስ ድረስ ጤና የለውም፤ ቍስልና እበጥ የሚመግልም ነው፤ አልፈረጠም፥ አልተጠገነም፥ በዘይትም አልለዘበም።
7. ምድራችሁ ባድማ ናት፤ ከተሞቻችሁ በእሳት ተቃጠሉ፤ እርሻችሁንም በፊታችሁ ሌሎች ይበሉታል፤ ባዕድ እንዳፈረሳት ምድር ባድማ ሆነች።
8. የጽዮንም ሴት ልጅ በወይን ቦታ እንዳለ ዳስ፥ በዱባ አትክልትም እንዳለ ጎጆ፥ እንደተከበበችም ከተማ ሆና ቀረች።
9. የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ፥ እንደ ሰዶም በሆንነ እንደ ገሞራም በመሰልነ ነበር።
10. እናንተ የሰዶም አለቆች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እናንተ የገሞራ ሕዝብ ሆይ፥ የአምላካችንን ሕግ አድምጡ።
11. የመሥዋዕታችሁ ብዛት ለእኔ ምን ይጠቅመኛል? ይላል እግዚአብሔር፤ የሚቃጠለውን የአውራ በግ መሥዋዕትንና የፍሪዳን ስብ ጠግቤያለሁ፤ የበሬና የበግ ጠቦት የአውራ ፍየልም ደም ደስ አያሰኘኝም።
12. በእኔ ፊት ልትታዩ ብትመጡ ይህን የመቅደሴን አደባባይ መርገጣችሁን ከእጃችሁ የሚሻ ማን ነው?
13. ምናምንቴውን ቍርባን ጨምራችሁ አታምጡ፤ ዕጣን በእኔ ዘንድ አጸያፊ ነው፤ መባቻችሁንና ሰንበታችሁን በጉባኤ መሰብሰባችሁን አልወድድም፤ በደልንም የተቀደሰውንም ጉባኤ አልታገሥም።
14. መባቻችሁንና በዓላቶቻችሁን ነፍሴ ጠልታለች፤ ሸክም ሆነውብኛል፥ ልታገሣቸውም ደክሜያለሁ።
15. እጃችሁንም ወደ እኔ ብትዘረጉ ዓይኔን ከእናንተ እሰውራለሁ፥ ልመናንም ብታበዙ አልሰማችሁም፤ እጆቻችሁ ደም ተሞልተዋል።
16. ታጠቡ ሰውነታችሁንም አንጹ፤ የሥራችሁን ክፋት ከዓይኔ ፊት አስወግዱ፤ ክፉ ማድረግን ተዉ፥
17. መልካም መሥራትን ተማሩ፥ ፍርድን ፈልጉ፥ የተገፋውን አድኑ፥ ለድሀ አደጉ ፍረዱለት ስለ መበለቲቱም ተምዋገቱ።
18. ኑና እንዋቀስ ይላል እግዚአብሔር፤ ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ብትሆን እንደ አመዳይ ትነጻለች፤ እንደ ደምም ብትቀላ እንደ ባዘቶ ትጠራለች።
19. እሺ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ፥ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤
20. እምቢ ብትሉ ግን ብታምፁም፥ ሰይፍ ይበላችኋል፤ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሮአልና።
21. ፍርድ ሞልቶባት የነበረው የታመነችይቱ ከተማ እንዴት ጋለሞታ ሆነች! ጽድቅ አድሮባት ነበር፥ አሁን ግን ገዳዮች አሉባት።
22. ብርሽ ወደ ዝገት ተለወጠ፤ የወይን ጠጅሽ ከውሃ ጋር ተደባለቀ።
23. አለቆችሽ አመጸኞችና የሌቦች ባልንጀሮች ሆኑ፤ ሁሉ ጉቦ ይወድዳሉ፥ ዋጋም ለማግኘት ይሮጣሉ፤ ለድሀ አደጉ አይፈርዱም፥ የመበለቲቱም ሙግት ወደ እነርሱ አይደርስም።
24. ስለዚህ የእስራኤል ኃያል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በጠላቶቼ ላይ ቍጣዬን እፈጽማለሁ፥ የሚቋቋሙኝንም እበቀላለሁ።
25. እጄንም በአንቺ ላይ አመጣለሁ፥ ዝገትሽንም በጣም አነጻለሁ፥ ቆርቆሮሽንም ሁሉ አወጣለሁ፤
26. ፈራጆችሽንም እንደ ቀድሞ አማካሪዎችሽንም እንደ መጀመሪያው ጊዜ መልሼ አስነሣለሁ፤ ከዚያም በኋላ የጽድቅ ከተማ የታመነችም ከተማ ተብለሽ ትጠሪያለሽ።
27. ጽዮን በፍርድ ከእርሷም የሚመለሱ በጽድቅ ይድናሉ።
28. በደለኞችና ኃጢአተኞች ግን በአንድነት ይሰበራሉ፥ እግዚአብሔርንም የሚተዉ ይጠፋሉ።
29. በወደዳችኋት የአድባር ዛፍ ታፍራላችሁና፥ ስለ መረጣችኋትም አትክልት እፍረት ይይዛችኋልና፤
30. ቅጠልዋ እንደ ረገፈ ዛፍ፥ ውሃም እንደሌለባት አትክልት ትሆናላችሁና።
31. ኃይለኛውም እንደ ተልባ ጭረት፥ ሥራውም እንደ ጠለሸት ይሆናል፤ አብረውም ይቃጠላሉ እነርሱንም የሚያጠፋ የለም።

      Isaiah (1/66)