| ← Hosea (9/14) → |
| 1. | እስራኤል ሆይ፥ ከአምላክህ ተለይተህ አመንዝረሃልና እንደ አሕዛብ ደስ አይበልህ፥ ሐሴትንም አታድርግ፤ በእህሉ አውድማ ሁሉ ላይ የግልሙትናን ዋጋ ወድደሃል። |
| 2. | አውድማውና መጥመቂያው አይመግባቸውም፥ ጉሽ ጠጅም ይጐድልባታል። |
| 3. | በእግዚአብሔር ምድር ላይ አይቀመጡም፤ ኤፍሬምም ወደ ግብጽ ይመለሳል፥ በአሦርም ርኩስን ነገር ይበላሉ። |
| 4. | ለእግዚአብሔርም የወይን ጠጅን ቁርባን አያፈስሱም፥ መሥዋዕታቸውም ደስ አያሰኘውም፤ የኀዘንም እንጀራ ይሆንላቸዋል፥ የሚበላውም ሁሉ ይረክሳል፤ እንጀራቸውም ለሰውነታቸው ይሆናል እንጂ ወደ እግዚአብሔር ቤት አይገባም። |
| 5. | በዓመት በዓል ቀንና በእግዚአብሔር በዓል ቀን ምን ታደርጋላችሁ? |
| 6. | እነሆ፥ ከጥፋት ሸሽተው ሄዱ፥ ግብጽም ትሰበስባቸዋለች፥ ሜምፎስም ትቀብራቸዋለች፤ ሳማም የብራቸውን ጌጥ ይወርሳል፥ እሾህም በድንኳኖቻቸው ውስጥ ይበቅላል። |
| 7. | የበቀል ወራት መጥቶአል፥ የፍዳም ወራት ደርሶአል፥ እስራኤልም ያውቃል፤ ከኃጢአትህና ከጠላትነትህ ብዛት የተነሣ ነቢዩ ሰንፎአል፥ መንፈስም ያለበት ሰው አብዶአል። |
| 8. | ኤፍሬም ከአምላኬ ጋር ተመልካች ነበረ፤ አሁን ግን ነቢዩ በመንገዱ ሁሉ ላይ የወፍ ወጥመድ ሆነ፥ በአምላኩም ቤት ጠላትነት አለ። |
| 9. | በጊብዓ ዘመን እንደ ነበረ እጅግ ረከሱ፤ እርሱም በደላቸውን ያስባል፥ ኃጢአታቸውንም ይበቀላል። |
| 10. | እስራኤልን በምድረ በዳ እንዳለ ወይን ሆኖ አገኘሁት፤ አባቶቻችሁንም ከመጀመሪያዋ ዓመት እንደ በለስ በkWraት ሆነው አየኋቸው፤ እነርሱ ግን ወደ ብዔልፌጎር መጡ፥ ለነውርም ተለዩ፥ እንደ ወደዱትም ርኩስ ሆኑ፥ |
| 11. | የኤፍሬምም ክብር እንደ ወፍ በርሮ ይጠፋል፤ መውለድና መፅነስ ማርገዝም አይሆንላቸውም። |
| 12. | ልጆቻቸውንም ቢያሳድጉ ሰው እንዳይቀርላቸው ልጅ አልባ አደረጋቸዋለሁ፤ ከእነርሱም በራቅሁ ጊዜ ወዮላቸው! |
| 13. | እኔ እንዳየሁ የኤፍሬም ልጆች ለምርኮ ተሰጥተዋል፤ ኤፍሬምም ልጆቹን ወደ ገዳዩች ያወጣል። |
| 14. | አቤቱ፥ ስጣቸው፤ ምን ትሰጣቸዋለህ? የሚጨነግፍን ማኅፀን የደረቀውንም ጡት ስጣቸው። |
| 15. | ክፋታቸው ሁሉ በጌልገላ አለ፤ በዚያ ጠልቻቸዋለሁ፤ ስለ ሠሩት ክፋት ከቤቴ አሳድዳቸዋለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲያ አልወድዳቸውም፤ አለቆቻቸው ሁሉ ዓመፀኞች ናቸው። |
| 16. | ኤፍሬም ተመታ፥ ሥሩም ደረቀ፥ ፍሬም አያፈራም፤ ደግሞም ቢወልዱ የማኅፀናቸውን ፍሬ እገድላለሁ። |
| 17. | አልሰሙትምና አምላኬ ይጥላቸዋል፤ በአሕዛብም መካከል ተቅበዝባዦች ይሆናሉ። |
| ← Hosea (9/14) → |