| ← Hosea (6/14) → |
| 1. | ኑ፥ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ፤ እርሱ ሰብሮናልና፥ እርሱም ይፈውሰናል፤ እርሱ መትቶናል፥ እርሱም ይጠግነናል። |
| 2. | ከሁለት ቀን በኋላ ያድነናል፤ በሦስተኛውም ቀን ያስነሣናል፥ በፊቱም በሕይወት እንኖራለን። |
| 3. | እንወቅ፤ እናውቀውም ዘንድ እግዚአብሔርን እንከተል፤ እንደ ወገግታም ተዘጋጅቶ እናገኘዋለን፤ እንደ ዝናብም ምድርንም እንደሚያጠጣ እንደ መጨረሻ ዝናብ ይመጣል። |
| 4. | ምሕረታችሁ እንደ ማለዳ ደመና፥ በማለዳም እንደሚያልፍ ጠል ነውና ኤፍሬም ሆይ፥ ምን ላድርግልህ? ይሁዳ ሆይ፥ ምን ላድርግልህ? |
| 5. | ስለዚህ በነቢያት እጅ ቈረጥኋቸው፥ በአፌም ቃል ገደልኋቸው፤ ፍርዴም እንደ ብርሃን ይወጣል። |
| 6. | ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን፥ ከሚቃጠልም መሥዋዕት ይልቅ እግዚአብሔርን ማወቅ እወድዳለሁና። |
| 7. | እነርሱ ግን እንደ አዳም ቃል ኪዳንን ተላልፈዋል፤ በዚያም ላይ ወንጅለውኛል። |
| 8. | ገለዓድ ኃጢአትን የሚሠሩ ሰዎች ከተማ፥ በደምም የተቀባ ነው። |
| 9. | ለሰውም እንደሚያደቡ ወንበዴዎች፥ እንዲሁ የካህናት ወገኖች በሴኬም መንገድ ላይ ይገድላሉ፤ ሴሰኝነትንም ያደርጋሉ። |
| 10. | በእስራኤል ቤት የሚያስፈራን ነገር አይቻለሁ፤ በዚያ በኤፍሬም ውስጥ ግልሙትና ተገኘ፥ እስራኤልም ረክሶአል። |
| 11. | ይሁዳ ሆይ፥ የሕዝቤን ምርኮ በምመልስበት ጊዜ ለአንተ ደግሞ መከር ተወስኖልሃል። |
| ← Hosea (6/14) → |