← Hosea (5/14) → |
1. | ካህናት ሆይ፥ ይህን ስሙ፤ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ አድምጡ፤ የንጉሥ ቤት ሆይ፥ ልብ አድርጉ፤ በምጽጳ ላይ ወጥመድ፥ በታቦርም ላይ የተዘረጋ አሽክላ ሆናችኋልና ፍርድ በእናንተ ላይ ነው። |
2. | ዓመፀኞችም እርድ አብዝተዋል፤ እኔ ግን እነዚያን ሁሉ እዘልፋለሁ። |
3. | ኤፍሬምን አውቀዋለሁ፥ እስራኤልም ከእኔ አልተሰወረም፤ ኤፍሬም ሆይ፥ ዛሬ አመንዝረሃል፥ እስራኤልም ረክሶአል። |
4. | ወደ አምላካቸው ይመለሱ ዘንድ ሥራቸውን አላቀኑም፤ የግልሙትና መንፈስ በውስጣቸው አለና፤ እግዚአብሔርንም አላውቁምና። |
5. | የእስራኤልም ትዕቢት በፊቱ ይመሰክራል፤ ስለዚህ እስራኤልና ኤፍሬም በኃጢአታቸው ይሰናከላሉ፤ ይሁዳም ደግሞ ከእነሱ ጋር ይሰናከላል። |
6. | እግዚአብሔርንም ለመሻት በጎቻቸውንና ላሞቻቸውን ነድተው ይሄዳሉ፤ ነገር ግን እርሱ ከእነርሱም ተመልሶአልና አያገኙትም። |
7. | ዲቃሎችን ልጆች ወልደዋልና እግዚአብሔርን ወንጅለዋል፤ አሁንም አንድ ወር እነርሱንና ርስታቸውን ይበላቸዋል። |
8. | በጊብዓ መለከትን፥ በራማ እንቢልታን ንፉና። ብንያም ሆይ፥ ከአንተ በኋላ እያላችሁ በቤትአዌን ላይ እሪ በሉ። |
9. | ኤፍሬም በዘለፋ ቀን የፈረሰ ይሆናል። በእስራኤል ነገዶች ዘንድ በእርግጥ የሚሆነውን ነገር ገልጫለሁ። |
10. | የይሁዳ አለቆች ድምበርን እንደሚነቅሉ ሆነዋል፤ እኔም መዓቴን እንደ ውኃ አፈስስባቸዋለሁ። |
11. | ኤፍሬም ከትእዛዝ በኋላ መሄድን ወድዶአልና የተገፋና በፍርድ የተጐዳ ሆኖአል። |
12. | እኔም ለኤፍሬም እንደ ብል፥ ለይሁዳም ቤት እንደ ነቀዝ ሆኜአለሁ። |
13. | ኤፍሬምም ደዌውን፥ ይሁዳም ቍስሉን ባየ ጊዜ ኤፍሬም ወደ አሦር ሄደ ወደ ንጉሡም ወደ ኢያሪም መልእክተኛን ላከ፤ እርሱ ግን ይፈውሳችሁ ዘንድ፥ ከቊስላችሁም ያድናችሁ ዘንድ አልቻለም። |
14. | እኔም ለኤፍሬም እንደ አንበሳ፥ ለይሁዳም ቤት እንደ አንበሳ ደቦል እሆናለሁና፤ እኔም ነጥቄ እሄዳለሁ እወስድማለሁ፥ የሚያድንም አይገኝም። |
15. | በደላቸውንም እስኪያውቁ ድረስ፥ ፊቴንም እስኪሹ ድረስ ሄጄ ወደ ስፍራዬ እመለሳለሁ፤ በመከራቸው ጊዜ እጅግ አድርገው ፊቴን ይፈልጋሉ። |
← Hosea (5/14) → |