← Hosea (2/14) → |
1. | የእስራኤልም ልጆች ቍጥር እንደማይሰፈርና እንደማይቈጠር እንደ ባሕር አሸዋ ይሆናል፤ እንዲህም ይሆናል፤ እናንተ ሕዝቤ አይደላችሁም ተብሎ በተነገረበት በዚያ ስፍራ የሕያው አምላክ ልጆች ይባላሉ። |
2. | የይሁዳ ልጆችና የእስራኤል ልጆች በአንድነት ይሰበሰባሉ፥ ለእነርሱም አንድ አለቃ ይሾማሉ፥ ከምድሪቱም ይወጣሉ፤ የኢይዝራኤል ቀን ታላቅ ይሆናልና። |
3. | ወንድሞቻችሁን። ዓሚ፥ እኅቶቻችሁንም። ሩሃማ በሉአቸው። |
4. | እናታችሁ ሚስቴ አይደለችምና፥ እኔም ባልዋ አይደለሁምና ተምዋገቱ፤ ከእናታችሁ ጋር ተምዋገቱ። ግልሙትናዋን ከፊትዋ፥ ምንዝርናዋንም ከጡቶችዋ መካከል ታስወግድ፤ |
5. | ዕራቁትዋን እንዳልገፍፋት፥ እንደ ተወለደችበትም ቀን እንዳላደርጋት፥ እንደ ምድረ በዳና እንደ ደረቅ ምድር እንዳላደርጋት፥ በጥማትም እንዳልገድላት፤ |
6. | የግልሙትናዋ ልጆች ናቸውና ልጆችዋን አልምርም። |
7. | እናታቸው አመንዝራለች፤ የፀነሰቻቸውም። እንጀራዬንና ውኃዬን፥ ጥጤንና የተልባ እግሬን፥ ዘይቴንና መጠጤን ከሚሰጡኝ ከውሽሞቼ በኋላ እሄዳለሁ ብላ አስነወረቻቸው። |
8. | ስለዚህ፥ እነሆ፥ መንገድሽን በእሾህ እዘጋለሁ፥ መንገድዋንም እንዳታገኝ ቅጥርን እቀጥርባታለሁ። |
9. | ውሽሞችዋንም ትከተላለች፥ ነገር ግን አትደርስባቸውም፤ ትፈልጋቸውማለች፥ ነገር ግን አታገኛቸውም፤ እርስዋም። ከዛሬ ይልቅ የዚያን ጊዜ ይሻለኝ ነበርና ተመልሼ ወደ ቀደመው ባሌ እሄዳለሁ ትላለች። |
10. | እርስዋም እህልንና ወይንን ጠጅ ዘይትንም የሰጠኋት፥ ለበኣልም የተሠራውን ብርና ወርቅ ያበዛሁላት እኔ እንደ ሆንሁ አላወቀችም። |
11. | ስለዚህ እህሌን በጊዜዋ፥ ወይን ጠጄንም በወረትዋ እወስዳለሁ፥ ዕራቁትነትዋንም እንዳትሸፍን ጥጤንና የተልባ እግሬን እገፍፋታለሁ። |
12. | አሁንም ውሽሞችዋ እያዩ ነውርዋን እገልጣለሁ፤ ከእጄም ማንም አያድናትም። |
13. | ደስታዋንም ሁሉ፥ በዓላቶችዋንም፥ መባቻዎችዋንም፥ ሰንበቶችዋንም፥ የተቀደሱትንም ጉባኤዎችን ሁሉ አስቀራለሁ። |
14. | እርስዋም። ውሽሞቼ የሰጡኝ ዋጋዬ ይህ ነው ያለችውን ወይንዋንና በለስዋን አጠፋለሁ፤ ዱርም አደርገዋለሁ፥ የምድረ በዳም አራዊት ይበሉታል። |
15. | እኔን ረስታ ውሽሞችዋን እየተከተለች፥ በጕትቾችዋና በጌጥዋም እያጌጠች ለበኣሊም ያጠነችበትን ወራት እበቀልባታለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። |
16. | ስለዚህ፥ እነሆ፥ አባብላታለሁ፥ ወደ ምድረ በዳም አመጣታለሁ፥ ለልብዋም እናገራለሁ። |
17. | ከዚያም የወይን ቦታዋን፥ የተስፋ በርም እንዲሆንላት የአኮርን ሸለቆ እሰጣታለሁ፤ በዚያም ከግብጽ ምድር እንደ ወጣችበት ቀን እንደ ሕፃንነትዋ ወራት ትዘምራለች። |
18. | በዚያ ቀን ባሌ ብለሽ ትጠሪኛለሽ እንጂ ዳግመኛ በኣሌ ብለሽ አትጠሪኝም፥ ይላል እግዚአብሔር፤ |
19. | የበኣሊምን ስም ከአፍዋ አስወግደዋለሁና፥ በስማቸውም እንግዲህ አይታሰቡምና። |
20. | በዚያም ቀን ከምድር አራዊትና ከሰማይ ወፎች ከመሬትም ተንቀሳቃሾች ጋር ቃል ኪዳን አደርግላቸዋለሁ፤ ቀስትንና ሰይፍን ሰልፍንም ከምድሩ እሰብራለሁ፥ ተከልለውም እንዲኖሩ አስተኛቸዋለሁ። |
21. | ለዘላለምም ለእኔ እንድትሆኚ አጭሻለሁ፤ በጽድቅና በፍርድ በምሕረትና በርኅራኄ አጭሻለሁ። |
22. | ለእኔም እንድትሆኚ በመታመን አጭሻለሁ፤ አንቺም እግዚአብሔርን ታውቂአለሽ። |
23. | በዚያንም ቀን እመልሳለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ለሰማይ እመልሳለሁ፥ ሰማይም ለምድር ይመልሳል፤ |
← Hosea (2/14) → |