← Hosea (13/14) → |
1. | ኤፍሬም በተናገረ ጊዜ ፍርሃት ነበረ፥ በእስራኤልም ዘንድ ታበየ፤ ነገር ግን በኣልን በማምለክ በበደለ ጊዜ ሞተ። |
2. | አሁንም ኃጢአትን ይሠሩ ዘንድ ጨመሩ፤ በብራቸውም ለራሳቸው ቀልጦ የተሠራ ምስልን፥ እንደ ጥበባቸውም ጣዖታትን ሠርተዋል፤ ሁሉም የሠራተኛ ሥራ ናቸው። ስለ እነርሱም። የሚሠዉ ሰዎች እምቦሳውን ይሳሙ ይላሉ። |
3. | ስለዚህም እንደ ማለዳ ደመና፥ በጥዋትም እንደሚያልፍ ጠል፥ በዐውሎ ነፍስም ከአውድማ እንደሚበተን እብቅ፥ ከመስኮትም እንደሚወጣ ጢስ ይሆናሉ። |
4. | እኔ ግን ከግብጽ ምድር ጀምሬ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ አታውቅም፥ ከእኔም በቀር ሌላ መድኃኒት የለም። |
5. | በምድረ በዳ፥ እጅግ በደረቀ ምድር አውቄህ ነበር። |
6. | ከተሰማሩ በኋላ ጠገቡ፥ በጠገቡም ጊዜ ልባቸው ታበየ፤ ስለዚህ ረሱኝ። |
7. | ስለዚህም እኔ እንደ አንበሳ ሆንሁባቸው፥ እንደ ነብርም በመንገድ አጠገብ አደባባቸዋለሁ፤ |
8. | ልጅዋ እንደ ተነጠቀባት ድብ እገጥማቸዋለሁ፥ የልባቸውንም ስብ እቀድዳለሁ፤ በዚያም እንደ አንበሳ እበላቸዋለሁ፥ የምድረ በዳም አውሬ ይነጣጠቃቸዋል። |
9. | እስራኤል ሆይ፥ በእኔ በረዳትህ ላይ በመነሣትህ ጥፋትህ ነው። |
10. | በየከተማህ ሁሉ ያድንህ ዘንድ ንጉሥህ ወዴት አለ? ስለ እነርሱም። ንጉሥንና አለቆችን ስጠኝ ብለህ የተናገርኸው መሳፍንቶችህ ወዴት አሉ? |
11. | በቍጣዬ ንጉሥን ሰጠሁህ፥ በመዓቴም ሻርሁት። |
12. | የኤፍሬም በደል ታስሮአል፥ ኃጢአቱም ተከማችቶአል። |
13. | ምጥ እንደ ያዛት ሴት ጭንቅ ይመጣበታል፤ በሚወለድበት ጊዜ በማኅፀን አፍ ቀጥ ብሎ አይወጣምና አእምሮ የሌለው ልጅ ነው። |
14. | ከሲኦል እጅ እታደጋቸዋለሁ፥ ከሞትም እቤዣቸዋለሁ፤ ሞት ሆይ፥ ቸነፈርህ ወዴት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ማጥፋትህ ወዴት አለ? ርኅራኄ ከዓይኔ ተሰወረች። |
15. | በወንድሞቹ መካከል ፍሬያማ ቢሆን የምሥራቅ ነፋስ ይመጣል፥ የእግዚአብሔር ነፋስ ከምድረ በዳ ይመጣል፤ ምንጩንም ያደርቃል፥ ፈሳሹንም ያጠፋል፥ የተከበሩ ዕቃዎች ሁሉ ያሉበትን መዝገብ ይበዘብዛል። |
16. | ሰማርያ በአምላክዋ ላይ ዐምፃለችና በደልዋን ትሸከማለች፤ በሰይፍ ይወድቃሉ፥ ሕፃኖቻቸውም ይፈጠፈጣሉ፥ እርጕዞቻቸውም ይቀደዳሉ። |
← Hosea (13/14) → |