← Hosea (10/14) → |
1. | እስራኤል ፍሬው የበዛለት የለመለመ ወይን ነው፤ እንደ ፍሬው ብዛት መሠዊያውን አብዝቶአል፤ እንደ ምድሩም ማማር መጠን ሐውልቶችን እያሳመሩ ሠርተዋል። |
2. | ልባቸው ተከፈለ፤ አሁንም በደላቸውን ይሸከማሉ፤ እርሱ መሠዊያቸውን ያፈርሳል፥ ሐውልቶቻቸውን ያጠፋል። |
3. | አሁንም። ንጉሥ የለንም፥ እግዚአብሔርን አልፈራንምና፤ ንጉሥስ ምን ያደርግልናል? ይላሉ። |
4. | የማይረባውን ቃል ይናገራሉ፤ ቃል ኪዳን በገቡ ጊዜ በሐሰት ይምላሉ፤ ስለዚህ መርዛም ሣር በእርሻ ትልም ላይ እንደሚበቅል መቅሠፍት ይበቅልባቸዋል። |
5. | የሰማርያ ሰዎች ስለ ቤትአዌን እምቦሳ ይፈራሉ፤ ክብሩም ከእርሱ ዘንድ ወጥቶአልና ሕዝቡ ያለቅሱለታል፥ የጣዖቱ ካህናትም በኀዘን ይንተባተባሉ። |
6. | ለንጉሡ ለኢያሪም እጅ መንሻ ይሆን ዘንድ ወደ አሦር ይማረካል፤ ኤፍሬምን እፍረት ይይዘዋል፥ እስራኤልም በምክሩ ያፍራል። |
7. | ሰማርያ ከንጉሥዋ ጋር በውኃ ላይ እንዳለ አረፋ ጠፍታለች። |
8. | የእስራኤል ኃጢአት የሆኑት የአዌን የኮረብታው መስገጃዎች ይፈርሳሉ፤ እሾህና አሜከላ በመሠዊያዎቻቸው ላይ ይበቅላል፤ ተራሮችንም። ክደኑን፥ ኮረብቶችንም። ውደቁብን ይሉአቸዋል። |
9. | እስራኤል ሆይ፥ ከጊብዓ ዘመን ጀምረህ ኃጢአትን ሠርተሃል፤ በዚያ ጸንተዋል፤ በጊብዓ ላይ ሰልፍ አይደርስባቸውምን? |
10. | በፈቀድሁም ጊዜ እገሥጻቸዋለሁ፤ ስለ ሁለቱም ኃጢአታቸው በታሰሩ ጊዜ አሕዛብ ይሰበሰቡባቸዋል። |
11. | ኤፍሬም ማበራየት እንደ ለመደች ጊደር ነው፥ እኔ ግን በአንገቱ ውበት እጫንበታለሁ፤ በኤፍሬም ላይ እጠምድበታለሁ፥ ይሁዳም ያርሳል፥ ያዕቆብም አፈሩን ያለሰልሳል። |
12. | እግዚአብሔር መጥቶ ጽድቅን እስኪያዘንብላችሁ ድረስ እርሱን የምትሹበት ዘመን ነውና ለእናንተ በጽድቅ ዝሩ፥ እንደ ምሕረቱም መጠን እጨዱ፥ ጥጋታችሁንም እረሱ። |
13. | ክፋትን አርሳችኋል፥ ኃጢአትንም አጭዳችኋል፥ የሐሰትንም ፍሬ በልታችኋል፤ በኃያላንህ ብዛት፥ በመንገድህም ላይ ታምነሃልና። |
14. | በሕዝብህም መካከል ሽብር ይነሣል፤ እናትም ከልጆችዋ ጋር በተፈጠፈጠች ጊዜ ሰልማን ቤትአርብኤልን በሰልፍ ቀን እንዳፈረሰ፥ አምባዎችህ ሁሉ ይፈርሳሉ። |
15. | ከኃጢአታችሁም ክፋት የተነሣ ቤቴል እንዲሁ ያደርግባችኋል፤ በነጋ ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ ፈጽሞ ይጠፋል። |
← Hosea (10/14) → |