| Hosea (1/14) → |
| 1. | በይሁዳ ነገሥታት በዖዝያንና በኢዮአታም በአካዝና በሕዝቅያስም ዘመን በእስራኤልም ንጉሥ በዮአስ ልጅ በኢዮርብዓም ዘመን ወደ ብኤሪ ልጅ ወደ ሆሴዕ የመጣ የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው። |
| 2. | እግዚአብሔር መጀመሪያ በሆሴዕ በተናገረ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ሆሴዕን። ምድሪቱ ከእግዚአብሔር ርቃ ታላቅ ግልሙትና ታደርጋለችና ሂድ፤ ጋለሞታን ሴትና የግልሙትናን ልጆች ለአንተ ውሰድ አለው። |
| 3. | እርሱም ሄዶ የዴቤላይምን ልጅ ጎሜርን አገባ፤ እርስዋም ፀነሰች ወንድ ልጅንም ወለደችለት። |
| 4. | እግዚአብሔርም። ከጥቂት ዘመን በኋላ የኢይዝራኤልን ደም በኢዩ ቤት ላይ እበቀላለሁና፥ ከእስራኤልም ቤት መንግሥትን እሽራለሁና ስሙን ኢይዝራኤል ብለህ ጥራው፤ |
| 5. | በዚያም ቀን በኢይዝራኤል ሸለቆ ውስጥ የእስራኤልን ቀስት እሰብራለሁ አለው። |
| 6. | ደግሞ ፀነሰች ሴት ልጅንም ወለደች። እግዚአብሔርም። ይቅር እላቸው ዘንድ የእስራኤልን ቤት ከእንግዲህ ወዲህ አልምርምና ስምዋን ሎሩሃማ ብለህ ጥራት፤ |
| 7. | ነገር ግን የይሁዳን ቤት እምራለሁ፤ በአምላካቸውም በእግዚአብሔር አድናቸዋለሁ እንጂ በቀስት ወይም በሰይፍ ወይም በሰልፍ ወይም በፈረሶች ወይም በፈረሰኞች አላድናቸውም አለው። |
| 8. | ሎሩሃማም ጡት ባስጣለች ጊዜ፥ ደግሞ ፀነሰች ወንድ ልጅንም ወለደች። |
| 9. | እግዚአብሔርም። ሕዝቤ አይደላችሁምና፥ እኔም አምላክ አልሆናችሁምና ስሙን ሎዓሚ ብለህ ጥራው አለው። |
| Hosea (1/14) → |