| Hebrews (1/13) → |
| 1. | ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ |
| 2. | ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤ |
| 3. | እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ፤ |
| 4. | ከመላእክት ይልቅ እጅግ የሚበልጥ ስምን በወረሰ መጠን እንዲሁ ከእነርሱ አብዝቶ ይበልጣል። |
| 5. | ከመላእክትስ። አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ፥ ደግሞም። እኔ አባት እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል |
| 6. | ያለው ከቶ ለማን ነው? ደግሞም በኵርን ወደ ዓለም ሲያገባ። የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉም ለእርሱ ይስገዱ ይላል። |
| 7. | ስለ መላእክትም። መላእክቱን መናፍስት አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል የሚያደርግ |
| 8. | ይላል፤ ስለ ልጁ ግን። አምላክ ሆይ፥ ዙፋንህ እስከ ዘላለም ድረስ ይኖራል፤ የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ነው። |
| 9. | ጽድቅን ወደድህ ዓመፅንም ጠላህ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ ከጓደኞችህ ይልቅ በደስታ ዘይት ቀባህ |
| 10. | ይላል። ደግሞ። ጌታ ሆይ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማዮችም የእጆችህ ሥራ ናቸው፤ |
| 11. | እነርሱም ይጠፋሉ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ፤ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፥ |
| 12. | እንደ መጎናጸፊያም ትጠቀልላቸዋለህ ይለወጡማል፤ አንተ ግን አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም |
| 13. | ይላል። ነገር ግን ከመላእክት። ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ |
| 14. | ከቶ ለማን ብሎአል? ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን? |
| Hebrews (1/13) → |