Habakkuk (1/3)  

1. ነቢዩ ዕንባቆም ያየው ሸክም ይህ ነው።
2. አቤቱ፥ እኔ ስጮኽ የማትሰማው እስከ መቼ ነው? ስለ ግፍ ወደ አንተ እጮኻለሁ፥ አንተም አታድንም።
3. በደልንስ ስለ ምን አሳየኸኝ? ጠማምነትንስ ስለ ምን ትመለከታለህ? ጥፋትና ግፍ በፊቴ ነው፤ ጠብና ክርክር ይነሣሉ።
4. ስለዚህ ሕግ ላልቶአል፥ ፍርድም ድል ነሥቶ አይወጣም፤ ኃጢአተኛ ጻድቅን ይከብባልና፤ ስለዚህ ፍርድ ጠማማ ሆኖ ይወጣል።
5. እናንተ የምትንቁ ሆይ፥ አንድ ቢተርክላችሁ ስንኳ የማታምኑትን ሥራ በዘመናችሁ እሠራለሁና እዩ፥ ተመልከቱ፥ ተደነቁ።
6. እነሆ፥ የእነርሱ ያልሆነውን መኖሪያ ይወርሱ ዘንድ በምድር ስፋት ላይ የሚሄዱትን መራሮችንና ፈጣኖችን ሕዝብ ከለዳውያንን አስነሣለሁ።
7. እነርሱ የሚያስፈሩና የሚያስደነግጡ ናቸው፤ ፍርዳቸውና ክብራቸው ከራሳቸው ይወጣል።
8. ፈረሶቻቸውም ከነብር ይልቅ ፈጣኖች ናቸው፥ ከማታም ተኵላ ይልቅ ጨካኞች ናቸው፤ ፈረሰኞቻቸውም ይንሳፈፋሉ፥ ከሩቅም ይመጣሉ፥ ለመብልም እንደሚቸኵል ንስር ይበርራሉ።
9. ሁሉም ለግፍ ሥራ ይመጣሉ፥ ፊታቸውንም እንደ ምሥራቅ ነፋስ ያቀናሉ፤ ምርኮኞችንም እንደ አሸዋ ይሰበስባሉ።
10. በነገሥታት ላይ ያላግጣሉ፥ መሳፍንትም ዋዛ ሆነውላቸዋል፤ በምሽጉ ሁሉ ይስቃሉ፥ አፈሩንም ከምረው ይወስዱታል።
11. የዚያን ጊዜም እንደ ነፋስ አልፎ ይሄዳል፥ ይበድልማል፤ ኃይሉንም አምላክ ያደርገዋል።
12. አቤቱ፥ የተቀደስህ አምላኬ ሆይ፥ አንተ ከዘላለም ጀምሮ አልነበርህምን? እኛ አንሞትም፤ አቤቱ፥ ለፍርድ ሠርተኸዋል፥ ለተግሣጽም አድርገኸዋል።
13. ዓይኖችህ ክፉ እንዳያዩ ንጹሐን ናቸው፥ ጠማምነትንም ትመለከት ዘንድ አትችልም፤ አታላዮችንስ ለምን ትመለከታለህ? ኃጢአተኛውስ ከእርሱ ይልቅ ጻድቅ የሆነውን ሲውጠው ስለ ምን ዝም ትላለህ?
14. ሰዎችንም እንደ ባሕር ዓሣዎች፥ አለቃም እንደሌላቸው ተንቀሳቃሾች ለምን ታደርጋቸዋለህ?
15. ሁሉን በመቃጥን ያወጣል፥ በመረቡም ይይዛቸዋል፥ በአሽክላውም ውስጥ ያከማቻቸዋል፤ ስለዚህ ደስ እያለው እልል ይላል።
16. እድል ፈንታው በእነርሱ ሰብታለችና፥ መብሉም በዝቶአልና ስለዚህ ለመረቡ ይሠዋል፥ ለአሽክላውም ያጥናል።
17. ስለዚህ መረቡን ይጥላልን? አሕዛብንም ዘወትር ይገድል ዘንድ አይራራምን?

      Habakkuk (1/3)