Genesis (9/50)  

1. እግዚአብሔርም ኖኅንና ልጆቹን ባረካቸው እንዲህም አላቸው። ብዙ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት።
2. አስፈሪነታችሁና አስደንጋጭነታችሁ በምድር አራዊት፥ በሰማይም ወፎች፥ በምድር ላይ በሚንቀሳቀሱትም፥ በባሕር ዓሦችም ሁሉ ላይ ይሁን፤ እነርሱም በእጃችሁ ተሰጥተዋል።
3. ሕይወት ያለው ተንቀሳቃሽ ሁሉ መብል ይሁናችሁ፤ ሁሉን እንደ ለመለመ ቡቃያ ሰጠኋችሁ።
4. ነገር ግን ነፍሱ ደሙ ያለችበትን ሥጋ አትብሉ፤
5. ነፍሳችሁ ያለችበትን ደማችሁን በእርግጥ እሻዋለሁ፤ ከአራዊት ሁሉ እጅ እሻዋለሁ፤ ከሰውም እጅ፥ ከሰው ወንድም እጅ፥ የሰውን ነፍስ እሻለሁ።
6. የሰውን ደም የሚያፈስስ ሁሉ ደሙ ይፈስሳል፤ ሰውን በእግዚአብሔር መልክ ፈጥሮታልና።
7. እናንተም ብዙ፥ ተባዙ፤ በምድር ላይ ተዋለዱ፥ እርቡባትም።
8. እግዚአብሔርም ለኖኅና ለልጆቹ እንዲህ ብሎ ተናገረ።
9. እኔም እነሆ ቃል ኪዳኔን ከእናንተና በኋላ ከሚመጣው ከዘራችሁ ጋር አቆማለሁ፤
10. ከእናንተ ጋር ላሉትም ሕያው ነፍስ ላላቸው ሁሉ፥ ከእናንተ ጋር ከመርከብ ለወጡት ለወፎች፥ ለእንስሳትም ለምድር አራዊትም ሁሉ፥ ለማንኛውም ለምድር አራዊት ሁሉ ይሆናል።
11. ቃል ኪዳኔንም ለእናንተ አቆማለሁ፤ ሥጋ ያለውም ሁሉ ዳግመኛ በጥፋት ውኃ አይጠፋም፤ ምድርንም ለማጥፋት ዳግመኛ የጥፋት ውኃ አይሆንም።
12. እግዚአብሔርም አለ። በእኔና በእናንተ መካከል፥ ከእናንተም ጋር ባለው በሕያው ነፍስ ሁሉ መካከል፥ ለዘላለም የማደርገው የቃል ኪዳን ምልክት ይህ ነው፤
13. ቀስቴን በደመና አድርጌአለሁ፥ የቃል ኪዳኑም ምልክት በእኔና በምድር መካከል ይሆናል።
14. በምድር ላይ ደመናን በጋረድሁ ጊዜ ቀስቲቱ በደመናው ትታያለች፤
15. በእኔና በእናንተ መካከል፥ ሕያው ነፍስ ባለውም ሥጋ ሁሉ መካከል ያለውን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ፤ ሥጋ ያለውንም ሁሉ ያጠፋ ዘንድ ዳግመኛ የጥፋት ውኃ አይሆንም።
16. ቀስቲቱም በደመና ትሆናለች፤ በእኔና በምድር ላይ በሚኖር ሥጋ ባለው በሕያው ነፍስ ሁሉ መካከል ያለውን የዘላለም ቃል ኪዳን ለማሰብ አያታለሁ።
17. እግዚአብሔርም ኖኅን። በእኔና በምድር ላይ በሚኖር ሥጋ ባለው ሁሉ መካከል ያቆምሁት የቃል ኪዳን ምልክት ይህ ነው አለው።
18. ከመርከብ የወጡት የኖኅ ልጆችም እነዚህ ናቸው፥ ሴም፥ ካም፥ ያፌት፤ ካምም የከነዓን አባት ነው።
19. የኖኅ ልጆች እነዚህ ሦስቱ ናቸው፤ ከእነርሱም ምድር ሁሉ ተሞላች።
20. ኖኅም ገበሬ መሆን ጀመረ፥ ወይንም ተከለ።
21. ከወይን ጠጁም ጠጣና ሰከረ፤ በድንኳኑም ውስጥ ዕራቁቱን ሆነ።
22. የከነዓን አባት ካምም የአባቱን ዕራቁትነት አየ፥ ወደ ውጭም ወጥቶ ለሁለቱ ወንድሞቹ ነገራቸው።
23. ሴምና ያፌትም ሸማ ወስደው በጫንቃቸው ላይ አደረጉ፥ የኋሊትም ሄደው የአባታቸውን ዕራቁትነት አለበሱ፤ ፊታቸውም ወደ ኋላ ነበረ፥ የአባታቸውንም ዕራቁትነት አላዩም።
24. ኖኅም ከወይን ጠጁ ስካር ነቃ፥ ታናሹ ልጁ ያደረገበትንም አወቀ።
25. እንዲህም አለ። ከነዓን ርጉም ይሁን፤ ለወንድሞቹም የባሪያዎች ባሪያ ይሁን።
26. እንዲህም አለ። የሴም አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ፥ ከነዓንም ለእነርሱ ባሪያ ይሁን።
27. እግዚአብሔርም ያፌትን ያስፋ፥ በሴምም ድንኳን ይደር፤ ከነዓንም ለእነርሱ ባሪያ ይሁን።
28. ኖኅም ከጥፋት ውኃ በኋላ ሦስት መቶ አምሳ ዓመት ኖረ።
29. ኖኅም የኖረበት ዘመን ሁሉ ዘጠኝ መቶ አምሳ ዓመት ሆነ፤ ሞተም።

  Genesis (9/50)