← Genesis (8/50) → |
1. | እግዚአብሔርም ኖኅን፥ በመርከብም ከእርሱ ጋር የነበረውን አራዊቱን ሁሉ፥ እንስሳውንም ሁሉ አሰበ፤ እግዚአብሔርም በምድር ላይ ነፋስን አሳለፈ፥ ውኃውም ጎደለ፤ |
2. | የቀላዩም ምንጮች የሰማይም መስኮቶች ተደፈኑ፥ ዝናብም ከሰማይ ተከለከለ፤ |
3. | ውኃውም ከምድር ላይ እያደር እያደር ቀለለ፥ ከመቶ አምሳ ቀንም በኋላ ውኃው ጎደለ። |
4. | መርከቢቱም በሰባተኛው ወር ከወሩም በአሥራ ሰባተኛው ቀን በአራራት ተራሮች ላይ ተቀመጠች። |
5. | ውኃውም እስከ አሥረኛው ወር ድረስ ይጎድል ነበር፤ በአሥረኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የተራሮቹ ራሶች ተገለጡ። |
6. | ከአርባ ቀንም በኋላ ኖኅ የሠራውን የመርከቢቱን መስኮት ከፈተ፥ |
7. | ቁራንም ሰደደው፤ እርሱም ወጣ፤ ውኃው ከምድር ላይ እስኪደርቅ ድረስ ወዲያና ወዲህ ይበር ነበር። |
8. | ርግብንም ውኃው ከምድር ፊት ቀልሎ እንደ ሆነ እንድታይ ከእርሱ ዘንድ ሰደዳት። |
9. | ነገር ግን ርግብ እግርዋን የምታሳርፍበት ስፍራ አላገኘችም፥ ወደ እርሱም ወደ መርከብ ተመለሰች፥ ውኃ በምድር ላይ ሁሉ ስለ ነበረ፤ እጁን ዘረጋና ተቀበላት፥ ወደ እርሱም ወደ መርከብ ውስጥ አገባት። |
10. | ከዚያም በኋላ ደግሞ እስከ ሰባት ቀን ቆየ፤ ርግብንም እንደ ገና ከመርከብ ሰደደ። |
11. | ርግብም በማታ ጊዜ ወደ እርሱ ተመለሰች፤ በአፍዋም እነሆ የለመለመ የወይራ ቅጠል ይዛ ነበር። ኖኅም ከምድር ላይ ውኃ እንደ ቀለለ አወቀ። |
12. | ደግሞ እስከ ሰባት ቀን ቆየ፤ ርግብንም ሰደዳት ዳግመኛም ወደ እርሱ አልተመለሰችም። |
13. | በኖኅ ዕድሜ በስድስት መቶ አንድ ዓመት በመጀመሪያው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ውኃው ከምድር ላይ ደረቀ፤ ኖኅም የመርከቢቱን ክዳን አነሣ፥ እነሆም፥ ውኃው ከምድር ፊት እንደ ደረቀ አየ። |
14. | በሁለተኛውም ወር ከወሩም በሀያ ሰባተኛው ቀን ምድር ደረቀች። |
15. | እግዚአብሔርም ለኖኅ እንዲህ ብሎ ነገረው። |
16. | አንተ ሚስትህንና ልጆችህን የልጆችህንም ሚስቶች ይዘህ ከመርከብ ውጣ። |
17. | ከአንተ ጋር ያሉትን አራዊት ሁሉ፥ ሥጋ ያላቸውን ሁሉ፥ ወፎችንና እንስሶችን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ከአንተ ጋር አውጣቸው፤ በምድር ላይ ይርመስመሱ፥ ይዋለዱ፥ በምድርም ላይ ይብዙ። |
18. | ኖኅም ልጆቹንና ሚስቱን የልጆቹንም ሚስቶች ይዞ ወጣ፤ |
19. | አራዊት ሁሉ፥ ተንቀሳቃሾች ሁሉ፥ ወፎችም ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚርመሰምሰው ሁሉ በየዘመዳቸው ከመርከብ ወጡ። |
20. | ኖኅም ለእግዚአብሔር መሠውያውን ሠራ፥ ከንጹሕም እንስሳ ሁሉ ከንጹሐን ወፎችም ሁሉ ወሰደ፥ በመሠውያውም ላይ መሥዋዕትን አቀረበ። |
21. | እግዚአብሔርም መልካሙን መዓዛ አሸተተ፤ እግዚአብሔርም በልቡ አለ። ምድርን ዳግመኛ ስለ ሰው አልረግምም፥ የሰው ልብ አሳብ ከታናሽነቱ ጀምሮ ክፉ ነውና፤ ደግሞም ከዚህ ቀድሞ እንዳደረግሁት ሕያዋንን ሁሉ እንደ ገና አልመታም። |
22. | በምድር ዘመን ሁሉ መዝራትና ማጨድ፥ ብርድና ሙቀት፥ በጋና ክረምት፥ ቀንና ሌሊት አያቋርጡም። a |
← Genesis (8/50) → |