← Genesis (6/50) → |
1. | እንዲህም ሆነ፤ ሰዎች በምድር ላይ መብዛት በጀመሩ ጊዜ ሴቶች ልጆች ተወለዱላቸው፤ |
2. | የእግዚአብሔር ልጆችም የሰውን ሴቶች ልጆች መልካሞች እንደ ሆኑ አዩ፤ ከመረጡአቸውም ሁሉ ሚስቶችን ለራሳቸው ወሰዱ። |
3. | እግዚአብሔርም። መንፈሴ በሰው ላይ ለዘላለም አይኖርም፥ እርሱ ሥጋ ነውና፤ ዘመኖቹም መቶ ሀያ ዓመት ይሆናሉ አለ። |
4. | በእነዚያ ወራት ኔፊሊም በምድር ላይ ነበሩ፤ ደግሞም ከዚያ በኋላ የእግዚአብሔር ልጆች የሰውን ሴቶች ልጆች ባገቡ ጊዜ ልጆችን ወለዱላቸው፤ እነርሱም በዱሮ ዘመን ስማቸው የታወቀ ኃያላን ሆኑ። |
5. | እግዚአብሔርም የሰው ክፉት በምድር ላይ እንደ በዛ፥ የልቡ አሳብ ምኞትም ሁልጊዜ ፈጽሞ ክፉ እንደ ሆነ አየ። |
6. | እግዚአብሔርም ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፥ በልቡም አዘነ። |
7. | እግዚአብሔርም። የፈጠርሁትን ሰው ከምድር ላይ አጠፋለሁ፥ ከሰው እስከ እንስሳ እስከ ተንቀሳቃሽም እስከ ሰማይ ወፍም ድረስ፤ ስለ ፈጠርኋቸው ተጸጽቼአለሁና አለ። |
8. | ኖኅ ግን በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን አገኘ። |
9. | የኖኅ ትውልድ እንዲህ ነው። ኖኅም በትውልዱ ጻድቅ ፍጹምም ሰው ነበረ፤ ኖኅ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ። |
10. | ኖኅም ሦስት ልጆችን ሴምን ካምን ያፌትንም ወለደ። |
11. | ምድርም በእግዚአብሔር ፊት ተበላሸች፤ ምድርም ግፍን ተሞላች። |
12. | እግዚአብሔርም ምድርን አየ፥ እነሆም ተበላሸች፤ ሥጋን የለበሰ ሁሉ በምድር ላይ መንገዱን አበላሽቶ ነበርና። |
13. | እግዚአብሔርም ኖኅን አለው። የሥጋ ሁሉ ፍጻሜ በፊቴ ደርሶአል፤ ከእነርሱ የተነሣ ምድር በግፍ ተሞልታለችና፤ እኔም እነሆ ከምድር ጋር አጠፋቸዋለሁ። |
14. | ከጎፈር እንጨት መርከብን ለአንተ ሥራ፤ በመርከቢቱም ጉርጆችን አድርግ፥ በውስጥም በውጭም በቅጥራን ለቅልቃት። |
15. | እርስዋንም እንዲህ ታደርጋታለህ፤ የመርከቢቱ ርዝመት ሦስት መቶ ክንድ፥ ወርድዋ አምሳ ክንድ፥ ከፍታዋ ሠላሳ ክንድ ይሁን። |
16. | ለመርከቢቱም መስኮትን ታደርጋለህ፤ ከቁመትዋም ክንድ ሙሉ ትተህ ጨርሳት፤ የመርከቢቱንም በር በጎንዋ አድርግ፤ ታችኛውንም ሁለተኛውንም ሦስተኛውንም ደርብ ታደርግላታለህ። |
17. | እኔም እነሆ ከሰማይ በታች የሕይወት ነፍስ ያለውን ሥጋ ሁሉ ለማጥፋት በምድር ላይ የጥፋት ውኃን አመጣለሁ፤ በምድር ያለው ሁሉ ይጠፋል። |
18. | ቃል ኪዳኔንም ከአንተ ጋር አቆማለሁ፤ ወደ መርከብም አንተ ልጆችህንና ሚስትህን የልጆችህንም ሚስቶች ይዘህ ትገባለህ። |
19. | ከአንተ ጋር በሕይወት ይኖሩ ዘንድ ሥጋ ካለው ከሕያው ሁሉ ሁለት ሁለት እያደረግህ ወደ መርከብ ታገባለህ፤ ተባትና እንስት ይሁን። |
20. | ከወፍ እንደ ወገኑ፥ ከእንስሳም እንደ ወገኑ፥ ከምድር ተንቀሳቃሽም ሁሉ እንደ ወገኑ በሕይወት ይኖሩ ዘንድ ሁለት ሁለት እየሆኑ ወደ አንተ ይግቡ። |
21. | ከሚበላውም መብል ሁሉ ለአንተ ውሰድ፥ ወደ አንተም ትሰበስባለህ፤ እርሱም ለአንተም ለእነርሱም መብል ይሆናል። |
22. | ኖኅም እንዲሁ አደረገ፤ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ አደረገ። a |
← Genesis (6/50) → |