| ← Genesis (50/50) |
| 1. | ዮሴፍም በአባቱ ፊት ወደቀ፥ በእርሱም ላይ አለቀሰ፥ ሳመውም። |
| 2. | ዮሴፍም ባለመድኃኒቶች አገልጋዮቹ አባቱን በሽቱ ያሹት ዘንድ አዘዘ፤ ባለመድኃኒቶችም እስራኤልን በሽቱ አሹት። |
| 3. | አርባ ቀንም ፈጸሙለት፤ የሽቱ መደረጊያው ወራት እንደዚሁ ይፈጸማልና፤ የግብፅም ሰዎች ሰባ ቀን አለቀሱለት። |
| 4. | የልቅሶውም ወራት ባለፈ ጊዜ ዮሴፍ ለፈርዖን ቤተ ሰቦች እንዲህ ብሎ ተናገረ። እኔ በፊታችሁ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆንሁ ለፈርዖን እንዲህ ብላችሁ ንገሩት። |
| 5. | አባቴ አምሎኛል እንዲህ ሲል። እነሆ እኔ እሞታለሁ፤ በቈፈርሁት መቃብር በከነዓን ምድር ከዚያ ቅበረኝ። አሁንም ወጥቼ አባቴን ልቅበርና ልመለስ። |
| 6. | ፈርዖንም። ውጣ፥ አባትህንም እንዳማለህ ቅበረው አለው። |
| 7. | ዮሴፍም አባቱን ሊቀብር ወጣ፤ የፈርዖን ሎላልትም ሁሉ ከእርሱ ጋር ወጡ፥ የቤቱ ሽማግሌዎችም የግብፅ ምድር ሽማግሌዎችም ሁሉ፤ |
| 8. | የዮሴፍም ቤተ ሰቦች ሁሉ ወንድሞቹም የአባቱም ቤተ ሰቦች ወጡ፤ ልጆቻቸውንና በጎቻቸውን ከብቶቻቸውን ብቻ በጌሤም ተዉ። |
| 9. | ሰረገሎችም ፈረሰኞችም ከእርሱ ጋር ወጡ፥ ሠራዊቱም እጅግ ብዙ ነበረ። |
| 10. | በዮርዳኖስ ማዶ ወዳለችው ወደ አጣድ አውድማ መጡ፥ እጅግ ታላቅ በሆነ በጽኑ ልቅሶም አለቀሱለት፤ ለአባቱም ሰባት ቀን ልቅሶ አደረገለት። |
| 11. | በዚያች ምድር የሚኖሩ የከነዓን ሰዎችም በአጣድ አውድማ የሆነውን ልቅሶ ባዩ ጊዜ። ይህ ለግብፅ ሰዎች ታላቅ ልቅሶ ነው አሉ፤ ስለዚህም የዚያን ቦታ ስም አቤል ምጽራይም ብለው ጠሩት፤ እርሱም በዮርዳኖስ ማዶ ነው። |
| 12. | ልጆቹም እንዳዘዛቸው እንደዚያው አደረጉለት፤ |
| 13. | ልጆቹም ወደ ከነዓን ምድር አጓዙት፥ ባለ ሁለት ክፍል በሆነች ዋሻም ቀበሩት፤ እርስዋም በመምሬ ፊት ያለች፥ አብርሃም ለመቃብር ርስት ከኬጢያዊ ከኤፍሮን ከእርሻው ጋር የገዛት ዋሻ ናት። |
| 14. | ዮሴፍና ወንድሞቹ አባቱንም ሊቀብሩ ከእርሱ ጋር የወጡት ሰዎች ሁሉ አባቱን ከቀበረ በኋላ ወደ ግብፅ ተመለሱ። |
| 15. | የዮሴፍም ወንድሞች አባታቸው እንደ ሞተ ባዩ ጊዜ እንዲህ አሉ። ምናልባት ዮሴፍ ይጠላን ይሆናል፥ ባደረግንበትም ክፋት ሁሉ ብድራት ይመልስብን ይሆናል። |
| 16. | ወደ ዮሴፍም መልእክት ላኩ እንዲህም አሉት። አባትህ ገና ሳይሞት እንዲህ ብሎ አዝዞአል። |
| 17. | ዮሴፍን እንዲህ በሉት። እባክህ የወንድሞችህን በደል ኃጢአታቸውንም ይቅር በል፥ እነርሱ በአንተ ከፍተውብሃልና፤ አሁንም እባክህ የአባትህ አምላክ ባሪያዎች የበደሉህን ይቅር በል። |
| 18. | ዮሴፍም ይህን ሲሉት አለቀሰ። ወንድሞቹ ደግሞ መጡ በፊቱም ሰግደው። እነሆ እኛ ለአንተ ባሪያዎችህ ነን አሉት። |
| 19. | ዮሴፍም አላቸው። አትፍሩ፤ እኔ በእግዚአብሔር ፋንታ ነኝን? |
| 20. | እናንተ ክፉ ነገርን አሰባችሁብኝ፤ እግዚአብሔር ግን ዛሬ እንደ ሆነው ብዙ ሕዝብ እንዲድን ለማድረግ ለመልካም አሰበው። |
| 21. | አሁንም አትፍሩ፤ እኔ እናንተንና ልጆቻችሁን እመግባችኋለሁ። አጽናናቸውም ደስ አሰኛቸውም። |
| 22. | ዮሴፍም በግብፅ ተቀመጠ፥ እርሱና የአባቱም ቤተ ሰብ፤ ዮሴፍም መቶ አሥር ዓመት ኖረ። |
| 23. | ዮሴፍም የኤፍሬምን ልጆች እስከ ሦስት ትውልድ አየ፤ የምናሴ ልጅ የማኪር ልጆችም በዮሴፍ ጭን ላይ ተወለዱ። |
| 24. | ዮሴፍም ወንድሞቹን አለ። እኔ እሞታለሁ፤ እግዚአብሔርም መጎብኘትን ይጎበኛችኋል፥ ከዚህችም ምድር ያወጣችኋል፤ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም ወደ ማለላቸው ምድር ያደርሳችኋል። |
| 25. | ዮሴፍም የእስራኤልን ልጆች። እግዚአብሔር ሲያስባችሁ አጥንቴን ከዚህ አንሥታችሁ ከእናንተ ጋር ውሰዱ ብሎ አማላቸው። |
| 26. | ዮሴፍም በመቶ አሥር ዓመት ዕድሜው ሞተ፤ በሽቱም አሹት፥ በግብፅ ምድር በሣጥን ውስጥ አኖሩት። |
| ← Genesis (50/50) |