| ← Genesis (49/50) → |
| 1. | ያዕቆብም ልጆቹን ጠርቶ እንዲህ አለ። በኋለኛው ዘመን የሚያገኛችሁን እንድነግራችሁ ተሰብሰቡ። |
| 2. | እናንት የያዕቆብ ልጆች ተሰብሰቡ፥ ስሙም፤ አባታችሁ እስራኤልንም አድምጡ። |
| 3. | ሮቤል፥ አንተ በኵር ልጄና ኃይሌ፥ የጕብዝናዬም መጀመሪያ ነህ፤ የክብር አለቃና የኃይል አለቃ። |
| 4. | እንደ ውኃ የምትዋልል ነህ፤ አለቅነት ለአንተ አይሁን፤ ወደ አባትህ መኝታ ወጥተሃልና፤ አረከስኸውም፤ ወደ አልጋዬም ወጣ። |
| 5. | ስምዖንና ሌዊ ወንድማማች ናቸው፤ ሰይፎቻቸው የዓመፃ መሣሪያ ናቸው። |
| 6. | በምክራቸው፥ ነፍሴ፥ አትግባ፤ ከጉባኤአቸውም ጋር፥ ክብሬ፥ አትተባበር፤ በቍጣቸው ሰውን ገድለዋልና፥ በገዛ ፈቃዳቸውም በሬን አስነክሰዋልና። |
| 7. | ቍጣቸው ርጉም ይሁን፥ ጽኑ ነበርና፤ ኵርፍታቸውም፥ ብርቱ ነበርና፤ በያዕቆብ እከፋፍላቸዋለሁ፥ በእስራኤልም እበታትናቸዋለሁ። |
| 8. | ይሁዳ፥ ወንድሞችህ አንተን ያመሰግኑሃል፤ እጅህ በጠላቶችህ ደንደስ ላይ ነው፤ የአባትህ ልጆች በፊትህ ይሰግዳሉ። |
| 9. | ይሁዳ የአንበሳ ደቦል ነው፤ ልጄ ሆይ፥ ከአደንህ ወጣህ፤ እንደ አንበሳ አሸመቀ፥ እንደ ሴት አንበሳም አደባ፤ ያስነሣውስ ዘንድ ማን ይችላል? |
| 10. | በትረ መንግሥት ከይሁዳ አይጠፋም፥ የገዥም ዘንግ ከእግሮቹ መካከል፥ ገዥ የሆነው እስኪመጣ ድረስ፤ የአሕዛብ መታዘዝም ለእርሱ ይሆናል። |
| 11. | ውርንጫውን በወይን ግንድ ያስራል፥ የአህያይቱንም ግልገል በወይን አረግ፤ ልብሱን በወይን ያጥባል፥ መጎናጸፊያውንም በወይን ደም። |
| 12. | ዓይኑም ከወይን ይቀላል፤ ጥርሱም ከወተት ነጭ ይሆናል። |
| 13. | ዛብሎን በባሕር ዳር ይቀመጣል፤ እርሱም ለመርከቦች ወደብ ይሆናል፤ ዳርቻውም እስከ ሲዶና ድረስ ነው። |
| 14. | ይሳኮር አጥንተ ብርቱ አህያ ነው፥ በበጎች ጕረኖም መካከል ያርፋል። |
| 15. | ዕረፍትም መልካም መሆንዋን አየ፥ ምድሪቱም የለማች መሆንዋን፤ ትከሻውን ለመሸከም ዝቅ አደረገ፥ በሥራም ገበሬ ሆነ። |
| 16. | ዳን በወገኑ ይፈርዳል፥ ከእስራኤል ነገድ እንደ አንዱ። |
| 17. | ዳን በጐዳና ላይ እንደ እባብ ይሆናል፥ በመንገድም እንደ ቀንዳም እባብ፤ ፈረሱን ከሰኮናው ይነክሳል፥ ፈረሰኛም ወደ ኋላው ይወድቃል። |
| 18. | እግዚአብሔር ሆይ፥ መድኃኒትህን እጠብቃለሁ። |
| 19. | ጋድን ዘማቾች ይዘምቱበታል፤ እርሱ ግን ተከታትሎ ይዘምትባቸዋል። |
| 20. | የአሴር እንጀራው ወፍራም ነው፥ ለነገሥታቱም ደስ የሚያሰኝ መብልን ይሰጣል። |
| 21. | ንፍታሌም የተፈታ ሚዳቋ ነው፤ መልካም ቃልን ይሰጣል። |
| 22. | ዮሴፍ ትንሹ የፍሬ ዛፍ ነው፥ በምንጭ አጠገብ የሚያፈራ የፍሬ ዛፍ፤ አረጎቹ በቅጥር ላይ ያድጋሉ። |
| 23. | ቀስተኞች አስቸገሩት፥ ነደፉትም፥ ተቃወሙትም፤ |
| 24. | ነገር ግን ቀስቱ እንደ ጸና ቀረ፤ የእጆቹም ክንድ በያዕቆብ አምላክ እጅ በረታ፥ በዚያው በጠባቂው በእስራኤል ዓምድ፥ |
| 25. | በአባትህ አምላክ እርሱም የሚረዳህ፥ ሁሉንም በሚችል አምላክ እርሱም የሚባርክህ፥ በሰማይ በረከት ከላይ በሚገኝ፥ በጥልቅም በረከት ከታች በሚሠራጭ፥ በጡትና በማኅፀን በረከት። |
| 26. | የአባትህ በረከቶች ጽኑዓን ከሆኑ ከተራሮች በረከቶች ይልቅ ኃያላን ናቸው፤ ዘላለማውያን ከሆኑ ከኮረፍቶችም በረከቶች ይልቅ ኃያላን ናቸው፤ እነርሱም በዮሴፍ ራስ ላይ ይሆናሉ፥ በወንድሞቹ መካከል አለቃ በሆነው ራስ አናት ላይ። |
| 27. | ብንያም ነጣቂ ተኵላ ነው፤ የበዘበዘውን በጥዋት ይበላል፥ የማረከውንም በማታ ይካፈላል። |
| 28. | እነዚህም ሁሉ አሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ናቸው፤ አባታቸው የነገራቸው ይህ ነው፥ ባረካቸውም፤ እያንዳንዳቸውን እንደ በረከታቸው ባረካቸው። |
| 29. | እንዲህ ብሎም አዘዛቸው። እኔ ወደ ወገኖቼ እሰበሰባለሁ፤ በኬጢያዊ በኤፍሮን እርሻ ላይ ባለችው ዋሻ ከአባቶቼ ጋር ቅበሩኝ፤ |
| 30. | እርስዋም በከነዓን ምድር በመምሬ ፊት ያለች፥ አብርሃም ለመቃብር ርስት ከኬጢያዊ ከኤፍሮን ከእርሻው ጋር የገዛት፥ ባለ ድርብ ክፍል ዋሻ ናት። |
| 31. | አብርሃምና ሚስቱ ሣራ ከዚያ ተቀበሩ፤ ይስሐቅና ሚስቱ ርብቃ ከዚያ ተቀበሩ፤ ከዚያም እኔ ልያን ቀበርኋት፤ |
| 32. | እርሻውና በእርስዋ ላይ ያለችው ዋሻ ከኬጢ ልጆች የተገዙ ናቸው። |
| 33. | ያዕቆብም ትእዛዙን ለልጆቹ ተናግሮ በፈጸመ ጊዜ እግሮቹን በአልጋው ላይ ሰብስቦ ሞተ፥ ወደ ወገኖቹም ተከማቸ። |
| ← Genesis (49/50) → |