| ← Genesis (48/50) → |
| 1. | ከዚህም ነገር በኋላ እንዲህ ሆነ፤ እነሆ አባትህ ታምሞአል ብለው ለዮሴፍ ነገሩት፤ እርሱም ሁለቱን ልጆቹን ምናሴንና ኤፍሬምን ይዞ ሄደ። |
| 2. | ለያዕቆብም። እነሆ ልጅህ ዮሴፍ መጥቶልሃል ብለው ነገሩት፤ እስራኤልም ተጠነካከረ፥ በአልጋውም ላይ ተቀመጠ። |
| 3. | ያዕቆብ ዮሴፍን አለው። ሁሉን የሚችል አምላክ በከነዓን ምድር በሎዛ ተገለጠልኝ፥ ባረከኝም |
| 4. | እንዲህም አለኝ። እነሆ ፍሬያማ አደርግሃለሁ፥ አበዛሃለሁም፥ ለብዙም ሕዝብ ጉባኤ አደርግሃለሁ፤ ይህችንም ምድር ከአንተ በኋላ ለዘላለም ርስት ለዘርህ እሰጣታለሁ። |
| 5. | አሁንም እኔ ወደ አንተ ከመምጣቴ በፊት በግብፅ ምድር የተወለዱልህ ሁለቱ ልጆችህ ለእኔ ይሁኑ፤ ኤፍሬምና ምናሴ ለእኔ እንደ ሮቤልና እንደ ስምዖን ናቸው። |
| 6. | ከእነርሱም በኋላ የምትወልዳቸው ልጆች ለአንተ ይሁኑ፤ በርስታቸው በወንድሞቻቸው ስም ይጠሩ። |
| 7. | እኔም ከመስጴጦምያ በመጣሁ ጊዜ፥ ወደ ኤፍራታ ለመግባት ጥቂት ቀርቶኝ በመንገድ ሳለሁ፥ ራሔል በከነዓን ምድር ሞተችብኝ፤ በዚያም በኤፍራታ መንገድ ላይ፥ እርስዋም ቤተ ልሔም ናት፥ ቀበርኋት። |
| 8. | እስራኤልም የዮሴፍን ልጆች አይቶ። እነዚህ እነማን ናቸው? አለው። |
| 9. | ዮሴፍም ለአባቱ። እግዚአብሔር በዚህ የሰጠኝ ልጆቼ ናቸው አለ። እርሱም። እባርካቸው ዘንድ ወደዚህ አቅርብልኝ አለ። |
| 10. | የእስራኤልም ዓይኖች ከሽምግልና የተነሣ ከብደው ነበር፥ ማየትም አይችልም ነበር፤ ወደ እርሱም አቀረባቸው፥ ሳማቸውም፥ አቀፋቸውም። |
| 11. | እስራኤልም ዮሴፍን። ፊትህን አያለሁ ብዬ አላሰብሁም ነበር፤ እነሆም እግዚአብሔር ዘርህን ደግሞ አሳየኝ አለው። |
| 12. | ዮሴፍም ከጕልበቱ ፈቀቅ አደረጋቸው፥ ወደ ምድርም በግምባሩ ሰገደ። |
| 13. | ዮሴፍም ሁለቱን ልጆቹን ወሰደ፥ ኤፍሬምንም በቀኙ በእስራኤል ግራ፥ ምናሴንም በግራው በእስራኤል ቀኝ አደረገው፥ ወደ እርሱም አቀረባቸው። |
| 14. | እስራኤልም ቀኝ እጁን ዘርግቶ በኤፍሬም ራስ ላይ አኖረው፥ እርሱም ታናሽ ነበረ፥ ግራውንም በምናሴ ራስ ላይ አኖረ፤ እጆቹንም አስተላለፈ፥ ምናሴ በኵር ነበርና። |
| 15. | ያዕቆብም ዮሴፍን ባረከ እንዲህም አለ። አባቶቼ አብርሃምና ይስሐቅ በፊቱ የሄዱለት እርሱ እግዚአብሔር፥ ከታናሽነቴ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እኔን የመገበኝ እግዚአብሔር፥ |
| 16. | ከክፉ ነገር ሁሉ ያዳነኝ መልአክ፥ እርሱ እነዚህን ብላቴኖች ይባርክ፤ ስሜም የአባቶቼ የአብርሃምና የይስሐቅም ስም በእነርሱ ይጠራ፤ በምድርም መካከል ይብዙ። |
| 17. | ዮሴፍም አባቱ ቀኝ እጁን በኤፍሬም ራስ ላይ ጭኖ ባየ ጊዜ አሳዘነው፤ የአባቱንም እጅ በምናሴ ራስ ላይ ይጭነው ዘንድ ከኤፍሬም ራስ ላይ አነሣው። |
| 18. | ዮሴፍም አባቱን። አባቴ ሆይ እንዲህ አይደለም፥ በኵሩ ይህ ነውና፤ ቀኝህን በራሱ ላይ አድርግ አለው። |
| 19. | አባቱም እንቢ አለ እንዲህ ሲል። አወቅሁ ልጄ ሆይ፥ አወቅሁ፤ ይህም ደግሞ ሕዝብ ይሆናል ታላቅም ይሆናል፤ ነገር ግን ታናሽ ወንድሙ ከእርሱ ይበልጣል፥ ዘሩም የአሕዛብ ሙላት ይሆናል። |
| 20. | በዚያም ቀን እንዲህ ብሎ ባረካቸው። በእናንተ እስራኤል እንዲህ ብሎ ይባርካል። እግዚአብሔር እንደ ኤፍሬምና እንደ ምናሴ ያድርግህ። ኤፍሬምንም ከምናሴ ፊት አደረገው። |
| 21. | እስራኤልም ዮሴፍን። እነሆ እኔ እሞታለሁ፤ እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋር ይሆናል፥ ወደ አባቶቻችሁም ምድር ይመልሳችኋል፤ |
| 22. | እኔም ከአሞራውያን በሰይፌና በቀስቴ የወሰድሁትን ለአንተ ከወንድሞችህ አንድ እጅ አብልጬ ሰጠሁህ አለው። a |
| ← Genesis (48/50) → |