| ← Genesis (47/50) → |
| 1. | ዮሴፍም ገባ ለፈርዖንም ነገረው እንዲህ ብሎ። አባቴና ወንድሞቼ በጎቻቸውም ላሞቻቸውም ያላቸውም ሁሉ ከከነዓን ምድር ወጡ፤ እነርሱም እነሆ በጌሤም ምድር ናቸው። |
| 2. | ከወንድሞቹም አምስት ሰዎችን ወስዶ በፈርዖን ፊት አቆማቸው። |
| 3. | ፈርዖንም ወንድሞቹን። ሥራችሁ ምንድር ነው? አላቸው። እነርሱም ፈርዖንን። እኛ ባሪያዎችህ፥ እኛም አባቶቻችንም፥ በግ አርቢዎች ነን አሉት። |
| 4. | ፈርዖንንም እንዲህ አሉት። በምድር ልንቀመጥ በእንግድነት መጣን፥ የባርያዎችህ በጎች የሚሰማሩበት ስፍራ የለምና፤ ራብ በከነዓን ምድር እጅግ ጸንቶአልና፤ አሁንም ባሪያዎችህ በጌሤም ምድር እንድንቀመጥ እንለምንሃለን። |
| 5. | ፈርዖንም ዮሴፍን ተናገረው እንዲህ ብሎ። አባትህና ወንድሞችህ መጥተውልሃል፤ |
| 6. | የግብፅ ምድር በፊትህ ናት፤ በመልካሙ ምድር አባትህንና ወንድሞችህን አኑራቸው፤ በጌሤም ምድር ይኑሩ፤ ከእነርሱም ውስጥ እውቀት ያላቸውን ሰዎች ታውቅ እንደ ሆነ በእንስሶቼ ላይ አለቆች አድርጋቸው። |
| 7. | ዮሴፍም ያዕቆብን አባቱን አስገብቶ በፈርዖን ፊት አቆመው፤ ያዕቆብም ፈርዖንን ባረከው። |
| 8. | ፈርዖንም ያዕቆብን። የዕድሜህ ዘመን ስንት ዓመት ነው? አለው። |
| 9. | ያዕቆብም ለፈርዖን አለው። የእንግድነቴ ዘመን መቶ ሠላሳ ዓመት ነው፤ የሕይወቴ ዘመኖች ጥቂትም ክፉም ሆኑብኝ፥ አባቶቼ በእንግድነት የተቀመጡበትንም ዘመን አያህሉም። |
| 10. | ያዕቆብም ፈርዖንን ባረከው ከፈርዖንም ፊት ወጣ። |
| 11. | ዮሴፍም አባቱንና ወንድሞቹን አኖረ፥ ፈርዖን እንዳዘዘም በግብፅ ምድር በተሻለችው በራምሴ ምድር ጉልትን ሰጣቸው። |
| 12. | ዮሴፍም ለአባቱና ለወንድሞቹ ለአባቱም ቤተ ሰዎች ሁሉ እንደ ልጆቻቸው መጠን እህል ሰጣቸው። |
| 13. | በምድርም ሁሉ እህል አልነበረም፥ ራብ እጅግ ጸንቶአልና፤ ከራብም የተነሣ የግብፅ ምድርና የከነዓን ምድር ተጎዳ። |
| 14. | ዮሴፍም ከግብፅ ምድርና ከከነዓን ምድር በእህል ሸመት የተገኘውን ብሩን ሁሉ አከማቸ፤ ዮሴፍም ብሩን ወደ ፈርዖን ቤት አስገባው። |
| 15. | ብሩም በግብፅ ምድርና በከነዓን ምድር አለቀ፤ የግብፅ ሰዎችም ሁሉ ወደ ዮሴፍ መጡ እንዲህ ሲሉ። እንጀራ ስጠን፤ ስለ ምን በፊትህ እንሞታለን? ብሩ አልቆብናልና። |
| 16. | ዮሴፍም። ከብቶቻችሁን አምጡልኝ፤ ብር ካለቀባችሁ በከብቶቻችሁ ፋንታ እህል እሰጣችኋለሁ አለ። |
| 17. | ከብቶቻቸውንም ወደ ዮሴፍ አመጡ፥ ዮሴፍም በፈረሶቻቸው በበጎቻቸውም በላሞቻቸውም በአህዮቻቸውም ፋንታ እህልን ሰጣቸው፤ በዚያች ዓመትም ስለ ከብቶቻቸው ሁሉ ፋንታ እህልን መገባቸው። |
| 18. | ዓመቱም ተፈጸመ፤ በሁለተኛውም ዓመት ወደ እርሱ መጥተው እንዲህ አሉት። እኛ ከጌታችን አንሰውርም፤ ብሩ በፍጹም አለቀ፥ ከብታችንም ከጌታችን ጋር ነው፤ ከሰውነታችንና ከምድራችን በቀር በጌታችን ፊት አንዳች የቀረ የለም፤ |
| 19. | እኛ በፊትህ ስለ ምን እንሞታለን? ምድራችንስ ስለ ምን ትጠፋለች? እኛንም ምድራችንንም በእህል ግዛን፥ እኛም ለፈርዖን ባሪያዎች እንሁን፥ ምድራችንም ለእርሱ ትሁን፤ እኛ እንድንድን እንዳንሞትም ምድራችንም እንዳትጠፋ ዘር ስጠን። |
| 20. | ዮሴፍም የግብፅን ምድር ሁሉ ለፈርዖን ገዛ፥ የግብፅ ሰዎች ሁሉ ራብ ስለ ጸናባቸው ርስታቸውን ሸጠዋልና፤ ምድሪቱ ለፈርዖን ሆነች። |
| 21. | ሕዝቡንም ሁሉ ከግብፅ ዳርቻ አንሥቶ እስከ ሌላው ዳርቻዋ ድረስ ባሪያዎች አደረጋቸው። |
| 22. | የካህናትን ምድር ብቻ አልገዛም፥ ካህናቱ ከፈርዖን ዘንድ ድርጎ ያገኙ ነበርና፥ ፈርዖንም የሰጣቸውን ድርጎ ይበሉ ነበር፤ ስለዚህም ምድራቸውን አልሸጡም። |
| 23. | ዮሴፍም ሕዝቡን እንዲህ አለ። እነሆ ዛሬ እናንተንና ምድራችሁን ለፈርዖን ገዝቻችኋለሁ፤ ዘር ውሰዱና ምድሪቱን ዝሩ፤ |
| 24. | በመከርም ጊዜ ፍሬውን ከአምስት እጅ አንዱን እጅ ለፈርዖን ስጡ፤ አራቱም እጅ ለእናንተ ለራሳችሁ፥ ለእርሻው ዘርና ለእናንተ ምግብ፥ ለቤተ ሰዋችሁና ለሕፃናቶቻችሁም ሲሳይ ይሁን። |
| 25. | እነርሱም። አንተ አዳነኸን፤ በጌታችን ፊት ሞገስን አናግኝ፥ ለፈርዖንም ባሪያዎች እንሆናለን አሉት። |
| 26. | ዮሴፍም ለፈርዖን ካልሆነችው ከካህናቱ ምድር በቀር አምስተኛው እጅ ለፈርዖን እንዲሆን በግብፅ ምድር እስከ ዛሬ ድረስ ሕግ አደረጋት። |
| 27. | እስራኤልም በግብፅ ምድር በጌሤም አገር ተቀመጠ፤ ገዙአትም፥ ረቡ፥ እጅግም በዙ። |
| 28. | ያዕቆብም በግብፅ ምድር አሥራ ሰባት ዓመት ተቀመጠ፤ የያዕቆብም ሙላው የሕይወቱ ዘመን መቶ አርባ ሰባት ዓመት ነው። |
| 29. | የእስራኤልም የሞቱ ቀን ቀረበ፤ ልጁን ዮሴፍንም ጠርቶ እንዲህ አለው። በፊትህ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆንሁ እጅህን ከጭኔ በታች አድርግ፥ በግብፅ ምድርም እንዳትቀብረኝ ምሕረትንና እውነትን አድርግልኝ፤ |
| 30. | ከአባቶቼም ጋር በተኛሁ ጊዜ ከግብፅ ምድር አውጥተህ ትወስደኛለህ፥ በመቃብራቸውም ትቀብረኛለህ። እርሱም። እንደ ቃልህ አደርጋለሁ አለ። |
| 31. | እርሱም። ማልልኝ አለው። ዮሴፍም ማለለት፤ እስራኤልም በአልጋው ራስ ላይ ሰገደ። |
| ← Genesis (47/50) → |