Genesis (46/50)  

1. እስራኤልም ለእርሱ ያለውን ሁሉ ይዞ ተነሣ፥ ወደ ቤርሳቤህ መጣ፥ መሥዋዕትንም ለአባቱ ለይስሐቅ አምላክ ሠዋ።
2. እግዚአብሔርም በሌሊት ራእይ። ያዕቆብ ያዕቆብ ብሎ ለእስራኤል ተናገረው። እርሱም። እነሆኝ አለ።
3. አለውም። የአባቶችህ አምላክ እግዚአብሔር እኔ ነኝ፤ ወደ ግብፅ መውረድ አትፍራ፥ በዚያ ትልቅ ሕዝብ አደርግሃለሁና።
4. እኔ ወደ ግብፅ አብሬህ እወርዳለሁ፥ ከዚያም ደግሞ እኔ አወጣሃለሁ፤ ዮሴፍም እጁን በዓይንህ ላይ ያኖራል።
5. ያዕቆብም ከቤርሳቤህ ተነሣ፤ የእስራኤልም ልጆች ያዕቆብን ይወስዱ ዘንድ ፈርዖን በሰደዳቸው ሰረገሎች አባታቸውን ያዕቆብንና ሕፃናቶቻቸውን ሴቶቻቸውንም ወሰዱ።
6. እንስሶቻቸውንም በከነዓን አገርም ያገኙትን ከብታቸውን ሁሉ ይዘው ያዕቆብና ዘሩ ሁሉ ከእርሱ ጋር ወደ ግብፅ መጡ፤
7. ወንዶች ልጆቹንና የልጆቹን ወንዶች ልጆች፥ ሴቶች ልጆቹንና የወንዶች ልጆቹን ሴቶች ልጆች፥ ዘሩንም ሁሉ ከእርሱ ጋር ወደ ግብፅ አስገባቸው።
8. ወደ ግብፅም የገቡት የእስራኤል ልጆች ስም ይህ ነው፥ ያዕቆብና ልጆቹ፤ የያዕቆብ በኵር ሮቤል።
9. የሮቤልም ልጆች፤ ሄኖኅ፥ ፈሉሶ፥ አስሮን፥ ከርሚ።
10. የስሞዖን ልጆች፤ ይሙኤል፥ ያሚን፥ ኦሃድ፥ ያኪን፥ ጾሐር፥ የከነዓናዊት ልጅ ሳኡል።
11. የሌዊም ልጆች፤ ጌድሶን፥ ቀዓት፥ ሜራሪ።
12. የይሁዳም ልጆች፤ ዔር፥ አውናን፥ ሴሎም፥ ፋሬስ፥ ዛራ፤ ዔርና አውናን በከነዓን ምድር ሞቱ፤ የፋሬስም ልጆች ኤስሮም፥ ሐሙል።
13. የይሳኮርም ልጆች፤ ቶላ፥ ፉዋ፥ ዮብ፥ ሺምሮን።
14. የዛብሎንም ልጆች፤ ሴሬድ፥ ኤሎን፥ ያሕልኤል።
15. ልያ በመስጴጦምያ በሶርያ ለያዕቆብ የወለደቻቸው ልጆችና ሴቲቱ ልጅዋ ዲና እነዚህ ናቸው፤ ወንዶችም ሴቶችም ልጆችዋ ሁሉ ሠላሳ ሦስት ነፍስ ናቸው።
16. የጋድም ልጆች ጽፎን፥ ሐጊ፥ ሹኒ፥ ኤስቦን፥ ዔሪ፥ አሮዲ፥ አርኤሊ።
17. የአሴርም ልጆች፤ ዪምና፥ የሱዋ፥ የሱዊ፥ በሪዓ፥ እኅታቸው ሤራሕ፤ የበሪዓ ልጆችም፤ ሔቤር፥ መልኪኤል።
18. ላባ ለልጁ ለልያ የሰጣት የዘለፋ ልጆች እነዚህ ናቸው፤ እነዚህን አሥራ ስድስቱንም ነፍስ ለያዕቆብ ወለደች።
19. የያዕቆብ ሚስት የራሔል ልጆች ዮሴፍና ብንያም ናቸው።
20. ለዮሴፍም በግብፅ ምድር ምናሴና ኤፍሬም ተወለዱለት፤ የሄልዮቱ ከተማ ካህን የጶጥፌራ ልጅ አስናት የወለደቻቸው ናቸው።
21. የብንያምም ልጆች፤ ቤላ፥ ቤኬር፥ አስቤል፤ የቤላ ልጆችም፤ ጌራ፥ ናዕማን፥ አኪ፥ ሮስ፥ ማንፌን፥ ሑፊም፤ ጌራም አርድን ወለደ።
22. ለያዕቆብ የተወለዱለት የራሔልም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ሁሉም አሥራ አራት ነፍስ ናቸው።
23. የዳንም ልጆች፤ ሑሺም።
24. የንፍታሌምም ልጆች፤ ያሕጽኤል፥ ጉኒ፥ ዬጽር፥ ሺሌም።
25. ላባ ለልጁ ለራሔል የሰጣት የባላ ልጆች እነዚህ ናቸው፤ እነዚህንም ለያዕቆብ ወለደችለት፤ ሁሉም ሰባት ነፍስ ናቸው።
26. ከያዕቆብ ጋር ወደ ግብፅ የገቡት ሰዎች ሁሉ ከጉልበቱ የወጡት፥ ከልጆቹ ሚስቶች ሌላ፥ ሁላቸው ስድሳ ስድስት ናቸው።
27. በግብፅ ምድር የተወለዱለት የዮሴፍም ልጆች ሁለት ናቸው፤ ወደ ግብፅ የገቡት የያዕቆብ ቤተ ሰዎች ሁሉ ሰባ ናቸው።
28. ይሁዳንም በጌሤም እንዲቀበለው በፊቱ ወደ ዮሴፍ ላከ፤ ወደ ጌሤም ምድርም ደረሱ።
29. ዮሴፍም ሰረገላውን አዘጋጀ፥ አባቱንም እስራኤልን ሊገናኘው ወደ ጌሤም ወጣ፤ ባየውም ጊዜ በአንገቱ ላይ ወደቀ፥ አቅፎትም ረጅም ጊዜ አለቀሰ።
30. እስራኤልም ዮሴፍን። አንተ ገና በሕይወት ሳለህ ፊትህን አይቼአለሁና አሁን ልሙት አለው።
31. ዮሴፍም ወንድሞቹንና የአባቱን ቤተ ሰዎች እንዲህ አላቸው። እኔ መጥቼ ለፈርዖን እንዲህ ብዬ እነግረዋለሁ። በከነዓን ምድር የነበሩት ወንድሞቼና የአባቴ ቤተ ሰዎች ወደ እኔ መጥተዋል፤
32. እነርሱም በግ የሚጠብቁ ሰዎች ናቸው፥ እንስሳ ያረቡ ነበርና፤ በጎቻቸውንና ላሞቻቸውን ያላቸውንም ሁሉ አመጡ።
33. ፈርዖንም ቢጠራችሁ። ተግባራችሁስ ምንድር ነው? ቢላችሁ፥
34. በግ ጠባቂ ሁሉ ለግብፅ ሰዎች ርኵስ ነውና በጌሤም እንድትቀመጡ እንዲህ በሉት። እኛ ባሪያዎችህ ከብላቴናነታችን ጀምረን እስከ አሁን ድረስ፥ እኛም አባቶቻችንም፥ እንስሳ አርቢዎች ነን። q ቍ@28፤ ጌሤም የሚለውን የግእዝ መጽሐፍ ራምሴ ይለዋል። a

  Genesis (46/50)